የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት፣ "መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ያነሰ ዓላማ የለውም። የተደራጀው በኢትዮጵያውያን፣ የሚመራው በኢትዮጵያውያን፣ የሚሠራው ለኢትዮጵያ ነው" የሚል ጥልቅ ትርጉም ያለው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይህ ንግግር የመከላከያ ሠራዊታችንን ተቋማዊ መሠረት፣ ዶክትሪን እና ስትራቴጂካዊ ግብ በአጭሩ የሚያስረዳ ከፍተኛ ሀገራዊ መልዕክት ነው።
ይህ ሐሳብ በዘመናዊ የመከላከያ ተቋም ግንባታ፣ በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲሁም በሀገራችን የውጭ እና የደኅንነት ፖሊሲ ውስጥ በተጨባጭ የሚንፀባረቅ እውነታን የያዘ ነው።
ሠራዊቱ "ከኢትዮጵያ ያነሰ ዓላማ የለውም" የሚለው መርሕ፣ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 87 የተጣለበትን የሀገር ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመጠበቅ አደራ ያመላክታል።
ተቋሙ በመከላከያ አዋጆች በተደነገገው መሠረት ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት እና ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ፣ ለሀገር እና ለሕዝብ ሕልውና ብቻ ዘብ እንዲቆም በሕግ የተረጋገጠ ብሔራዊ ጋሻ ነው።
"በኢትዮጵያውያን የተደራጀ" መሆኑ ደግሞ በበርካታ የሪፎርም ስኬቶቹ ይገለጻል። በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ፍትሐዊ ስብጥር እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎ ከማረጋገጡ ባለፈ፣ ሀገራችንን ከዘመናዊ የፀጥታ ስጋቶች ለመጠበቅ የሚያስችል ሰፊ መዋቅር ተዘርግቶለታል።
90 የስኬት ዓመታትን ያሳለፈው አየር ኃይላችን፣ ዳግም የተደራጀው የባሕር ኃይል፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ በእጅጉ የታገዘው የምድር ጦር፣ የሳይበር እና የስፔስ አቅም ግንባታ የዚህ ዘመናዊ አደረጃጀት ማሳያዎች ናቸው።
ከዚህም ባሻገር ሠራዊቱ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት እና በመጠገን የጀመረው ሀገራዊ አቅም ግንባታ ተቋሙን ይበልጥ አጠናክሮታል።
"በኢትዮጵያውያን የሚመራ" መሆኑ የሚሰጠው አንድምታ፣ በዴሞክራሲያዊ የሲቪል ቁጥጥር እና በሀገር በቀል ወታደራዊ አመራር ግንባታ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው።
የመከላከያ ሚኒስትር ሲቪል እንዲሆን በሕግ መወሰኑ፣ ሠራዊቱ በሕዝብ በተመረጠ አስተዳደር ስር መሆኑን ያረጋግጣል።
በሌላ በኩል ዋና ኢታማዦር ሹሙን ጨምሮ የዕዝ አመራሮች፣ በኢፌዴሪ መከላከያ ጦር ኮሌጅ እና በሌሎች ሀገር ውስጥ የማሠልጠኛ ተቋማት በበቁ ሀገር በቀል ወታደራዊ ባለሙያዎች እየተመሩ ይገኛሉ።
ሠራዊቱ "የሚሠራው ለኢትዮጵያ ነው" የሚለው መርሕ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተግባር የተረጋገጠ እውነት ነው።
በሀገር ውስጥ የሕዝብን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር፣ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ስትራቴጂያዊ የልማት አውታሮችን ከተፈጥሮ እና ከሰው ሠራሽ አደጋዎች ይጠብቃል፤ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በግብርና ልማት ሥራዎች ላይም ግንባር ቀደም ተሳትፎ ያደርጋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት ሥር ያከናወናቸው የሰላም ማስከበር ተግባራት የኢትዮጵያን ሀገራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ ከፍ ያደረጉ ደማቅ ታሪኮች ናቸው።
በአጠቃላይ መከላከያ ሠራዊታችን ከሕዝብ የወጣ፣ ለሕዝብ የሚኖር የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው!
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: