Search

ከስሜት ፖለቲካ ወደ እስትራቴጂያዊ ስሌት

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 78

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ መጠይቅ ያነሷቸው ሀሳቦች፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትርክት ከሥረ መሠረቱ ለማረም እና ጠንካራ የተቋማዊ ግንባታ አቅጣጫን ለማመላከት የተሰነዘሩ ጥልቅ መልዕክቶች ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አንኳር ሀሳቦች ከሀገራችን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማዋሃድ ቀጣዮቹን ነጥቦች እናነሳለን፡፡

የሀገር ግንባታ ትርክትን የማረም ፖለቲካዊ ርምጃ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ፈተና ሕዝብን የሚያጋጭ የሐሰት ትርክት ነው፡፡ ይህን ስብራት ለመጠገን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን (በተለይም የአማራ እና የኦሮሞን) ታሪካዊ መስተጋብር በጋብቻና በፖለቲካዊ ውህደት መነጽር አቅርበውታል፡፡

ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን በማርገብ ማዕከላዊ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ማጠናከር የግድ ይላል፡፡ ይህም ከመደመር እሳቤና ከዓድዋ ድል መታሰቢያ የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ጋር በቀጥታ ይናበባል፡፡

የፖለቲካ ምህዳሩ መከፈት እና የሰኔ 15 አሳዛኝ ክስተት ትምህርት

የዴሞክራሲ ሽግግር ፈታኝ ነው፡፡

የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትና የሚዲያ ነፃነት ለዴሞክራሲያዊ ጉዞ ቁርጠኝነትን ያሳያል፡፡

ሆኖም "ንጹህ አየር ለማስገባት መስኮት ሲከፈት አብረው የሚገቡ ትንኞች አሉ" እንዳሉት፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ባልጎለበቱበት ማኅበረሰብ የሰኔ 15ቱን የመሰሉ አሳዛኝ ክስተቶች መፈጠራቸው በኃይል ሥልጣን የመያዝ አባዜ አሁንም መኖሩን ያሳያል፡፡

በመሆኑም ፈጣን የፖለቲካ ለውጥ ከከፍተኛ ጥንቃቄ ጋር መጓዝ አለበት፡፡

የማንነት ጥያቄዎችን በተቋማዊ ጥበብ መመለስ

እንደ ወልቃይት ያሉ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎችን በአቋራጭ መንገድ መፍታት አደገኛ ነው፡፡

መንግሥት ይህን ተረድቶ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱ የጎለመሰ ተቋማዊ አሠራር ዝግጁነትን ያሳያል፡፡

መፍትሔዎቹ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ሀገራዊ መግባባትን የሚጠይቁ እንጂ በስሜት የሚፈጸሙ መሆን የለባቸውም፡፡

ከባህል ወደ ተቋም፡ የኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር

የሀገር ግንባታ በፖለቲካ ብቻ አይሳካም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር በቀል ዕውቀትን (ቅኔ፣ ደቦ፣ ገዳ) ከዘመናዊ ተቋማዊ አሠራር ጋር አቆራኝተዋል፡፡ ይህ እሳቤ ከመሠረተ ልማት እና ከንግድ ኮሪደር ፕሮጀክቶች ጋር ሲዋሃድ የኢትዮጵያን አዲስ ገጽታ ይስላል፡፡ በተጨማሪም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) መሠረት ያደረጉ የዲጂታል አስተዳደር ትግበራዎች ከፖለቲካዊ መረጋጋት ጋር የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡

የዲያስፖራው ፖለቲካ፡ ከምናባዊ ዓለም ወደ መሬት የወረደ ተሳትፎ

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተሳትፎ ከሀገር ግንባታ ይልቅ በግል ጥቅም እና በተሳሳተ ስሌት ላይ የተመሠረተ መሆኑ በቃለ መጠይቁ ተጋልጧል፡፡ መንግሥት የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በማቋቋም ጥረት ቢያደርግም፣ አሁንም በስሜት መነዳትና ከእውነታው መራቅ በስፋት ይስተዋላል፡፡

በአጠቃላይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዕከላዊ መልዕክት ኢትዮጵያን የመገንባቱ ሂደት ታሪካዊ እውነታዎችን ከመቀበል፣ ተቋማትን ከማሳደግና ከስሜት ፖለቲካ በመላቀቅ ሥሌት ወዳለው አካሄድ ከመሸጋገር ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ነው፡፡

ወጣቱና የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ከምናባዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦርነት ወጥተው በመድረኩ አዎንታዊ ተሳትፎ ማድረግ የዘመኑ ግዴታቸው ነው፤ ጠንካራዋ ኢትዮጵያ የሁላችንንም የደቦ ሥራ በጥብቅ ትጠይቃለችና፡፡

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: