Search

ከቃል ባሻገር የታየ ሀገራዊ ብቃት፡ ትላልቅ ህልሞችን የማሳካት ታሪካዊ ጉዞ

ማክሰኞ ሐምሌ 28, 2018 45

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ትላልቅ ነገሮችን አቅዳ ሕዝቦቿን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ማሳያ ነው" ሲሉ የተናገሩት ሀሳብ በትላንትናው ዕለት መላ ኢትዮጵያንን ባንቀሳቀሰው ግዙፍ ንቅናቄ በተግባር ተረጋገጧል።

ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድ ልብ ተነስተው ያከናወኑት የችግኝ ተከላ ሀገራችን በጽናት ከተነሳች እና ሕዝቧን በአንድነት አስተባብራ ከተንቀሳቀሰች ማንኛውንም ግዙፍ ሀገራዊ ህልም ማሳካት እንደምትችል ለዓለም ያስመሰከረችበት ታሪካዊ ዕለት ሆኗል።

በዕለቱ የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ተከላ ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብን አቅም እና ቁርጠኝነት ያሳየ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ከማለዳው ጀምሮ በየተራራው፣ በየሸለቆው እና በየከተሞች አደባባይ የታየው ሕዝባዊ መነቃቃት የሀገራዊ ኅብረታችንን ጥንካሬ በግልጽ ያሳየ ነበር።

ይህ በትላንትናው ዕለት በየቦታው የተተከለው አረንጓዴ ዐሻራ ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር፣ በምግብ ራሷን የቻለች እና ለተፈጥሮ ሀብቷ ተቆርቋሪ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ትልቅ ራእይ በተግባር የተተረጎመበት ነው።

ይህ ታላቅ ስኬት ሙሉ የሚሆነው ከመትከል ባሻገር በሚደረገው ዘላቂ ጥረት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ችግኝ መትከል የመጀመሪያው እና ወሳኙ እርምጃ ቢሆንም፣ ዋናውና ትልቁ ትኩረታችን መሆን ያለበት በተተከሉት ችግኞች እንክብካቤ ላይ ነው። እያንዳንዷ የተተከለች ችግኝ ተንከባካቢ እና ጠባቂ ሊኖራት ይገባል።

ችግኞቹ ፀድቀው፣ አድገው እና ጥላ እና ፍሬ ሆነው እስኪታዩ ድረስ የማኅበረሰቡ፣ የተቋማት እና የየአካባቢው ዜጎች የቅርብ ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል።

የዚህ ኅበረታችን የመጨረሻው ስኬት የሚለካው በኅበረት ወጥተን ችግኞቹን እንደተከልናቸው ሁሉ አድገው በጸደቁት እና የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር በቀየሩት ዛፎች መጠን ነው::

ዛሬ በየምድሩ የተተከሉት ሚሊዮን ችግኞች የነገዋ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የአካባቢ ጥበቃ ሀብቶች ናቸው።

በመሆኑም ከዚህ የተከላ ንቅናቄ ማጠቃለያ በኋላ እያንዳንዱ ዜጋ የተተከሉትን ችግኞች የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና የማሳደግ ሀገራዊ ኃላፊነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ዛሬ በላባችን ያራሰነው አፈር እና የተከልነው ችግኝ ነገ ለሀገራችን ለምለምነት፣ ለንጹህ አየር እና ለቀጣዩ ትውልድ አስተማማኝ ሕይወት ዋስትና ሆኖ ይኖራል።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: