በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባምባሲ ከተማ የተገነባው 3ኛው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ክፍት ሆኗል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የተጀመረው የመሶብ ማዕከላት አደረጃጀት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግና የተገልጋዩን እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ትልቅ አቅም ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፣ ቀደም ሲል ተመርቀው ሥራ የጀመሩት የቤጉ እና የአሶሳ የመሶብ ማዕከላት ከ46 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት መስጠታቸውንና የተገልጋዮችን እርካታ ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ 3 ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማዕከላቱን ቁጥር ወደ 5 ለማድረስ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የባምባሲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፈይሰል ዓሊ በበኩላቸው፤ የማዕከሉ መከፈት ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት የተገልጋዮችን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ በመሆኑ የሕዝቡን አጣዳፊ የአገልግሎት ጥያቄዎች ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
በዛሬውዕለት በባምባሲ ከተማ ሥራ የጀመረው አዲሱ መሶብ ማዕከል ከ4 የከተማ ጽሕፈት ቤቶች 29 አገልግሎቶችን፤ ከ3 የልማት መሥሪያ ቤቶች 7 አገልግሎቶችን በድምሩ 36 የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለህዝብ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በነስረዲን አህመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: