የኩታ ገጠም (ክላስተር) እርሻዎችን ወደ አግሪ-ቢዝነስ ኩባንያዎች የማሸጋገር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የኩታ ገጠም እርሻ በመደመር እሳቤ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች በማደራጀት፣ የመሬት ይዞታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የእርሻ ሥራቸውን በጋራ አቀናጅተው የሚያለሙበት አሠራር ነው።
አሠራሩ አርሶ አደሮች ተደራጅተው የግብርና ሜካናይዜሽንን፣ ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያን እና አግሮ-ኬሚካሎችን በመጠቀም ምርታማነትን እንዲያሳድጉ እና ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በ2011 ዓ.ም በ600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የክላስተር እርሻ፣ በ2018 ዓ.ም 13 ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ በአሁኑ ወቅት 9.5 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በክላስተር እርሻ ተደራጅተው ማሳቸውን እያለሙ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም 29 በመቶ የምርታማነት ዕድገት ማስመዘገብ መቻሉን አስረድተዋል።
እነዚህን የክላስተር እርሻዎች አዲስ በወጣው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያዎች አዋጅ መሠረት በሕግ የተመዘገቡ እና በሙያ የሚተዳደሩ የአርሶ አደሮች አግሪ-ቢዝነስ ኩባንያዎች እንዲሆኑ የማሸጋገር እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ይህም የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር እና የግብርናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ተወዳዳሪነት ለማሸጋገር የሚረዳ መሆኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባስተላለፉት መክዕክት አስገንዝበዋል።
አዲስ የሚቋቋሙት የአርሶ አደሮች የቢዝነስ ኩባንያዎች የአነስተኛ አምራቾችን የቢዝነስ ዕሳቤ በማስፋት ምርት የማሰባሰብ፣ እሴት የመጨመር እና በገበያ የመደራደር አቅማቸውን እንደሚያሳድጉ አመልክተዋል።
በተጨማሪም አነስተኛ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ወደ መካከለኛ አልሚነት እና አግሮ-ፕሮሰሲንግ ሥራዎች እንዲሸጋገሩ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት የሚፈጥር መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: