Search

ኢትዮጵያ ገና ያልተነካ ከፍተኛ የቱሪዝም እምቅ ሀብት ያላት ሀገር ናት - ሲኤን ኤን

ማክሰኞ ሐምሌ 28, 2018 36

ኢትዮጵያ ገና ያልተነካ ከፍተኛ የቱሪዝም ዕምቅ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን ሲኤንኤን በሰፊው ዘግቧል።

የተፈጥሮ ሀብቶቿን ለዓለም ለማስተዋወቅም ሰፊ እቅድ ይዛ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝም የፕሮግራሙ አዘጋጅ በልዩ ቅኝቷ ዳስሳለች።

ዘገባው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለያዘችው ትልቅ የቱሪዝም እቅድ እና በዘርፉ እያስመዘገበች ስላለው ተጨባጭ ውጤት፣ በቅርቡ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በዋና ማሳያነት አቅርቧል።

የፕሮግራሙ አቅራቢ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ የያዘውን እጅግ አስደናቂ የተፈጥሮ ብዝኃ ሕይወት እና የአንድን አነስተኛ ሀገር ስፋት የሚሸፍን ግዙፍ መልክዓ ምድርን በማድነቅ ለተመልካቾች አጋርታለች።

በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው ይህ አስደናቂ ፓርክ፣ ከባሕር ወለል በላይ 1 ሺህ 800 እስከ 4 ሺህ 385 ሜትር ከፍታ ባላቸው ማራኪ የመሬት አቀማመጦች የተሸፈነ ነው።

አጠቃላይ የቆዳ ስፋቱም 2 ሺህ 150 እስከ 2 ሺህ 220 ካሬ ኪሎ ሜትር ያካልላል። በፓርኩ ውስጥ 4 ሺህ 385 ሜትር ከፍታ ያለውና የሀገራችን ሁለተኛው ረጅሙ ቱሉ ዲምቱ ተራራ፣ ሰፊው የሰናቴ አፍሮ-አልፓይን ፕላቶ፣ ምስጢራዊው የሀረና ደን እና ልዩ ቅርጽ ያለው የራፉ የድንጋይ ደን ይገኛሉ።

ከዚህም ባሻገር ፓርኩ 80 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት ዝርያዎችን በውስጡ አቅፎ የያዘ ሲሆን፣ ከእነዚህ ዝርያዎች ውስጥ 22 በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መሆናቸውን ዘገባው አብራርቷል።

ይህን ድንቅ ሀብት የያዘውን ፓርክ እና አካባቢውን ለቱሪስቶች ይበልጥ ምቹ እና ተደራሽ ለማድረግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የሲኤንኤን ዘገባ እማኝነቱን አስቀምጧል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከፕሮግራሙ አዘጋጅ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱሪዝም አማካሪ ሚኒስትር ክቡር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን እንዲሁም ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት ማሟላት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ለአፍሪካ ገበያ ቅድሚያ በመስጠት፣ አፍሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ በቀላሉ መምጣት የሚችሉበትን እና ቆይታቸውን ማራዘም የሚያስችላቸውን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለዚህም ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምቹ ሆቴሎች እና ሎጆች፣ እንዲሁም ወደ ብሔራዊ ፓርኮች የሚያቀኑ ጥራት ያላቸው የመንገድ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በናትናኤል ፀጋዬ

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: