ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጀመረችው አጠቃላይ የኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ እየሳበ ይገኛል።
ታዋቂው የዓለም አቀፍ የዜና መረብ ሲኤንኤን (CNN) በቅርቡ «Connecting Africa» በተሰኘው ልዩ ዝግጅቱ፣ በጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ሩቤዲሪ አቅራቢነት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ለውጥ በስፋት ዳስሷል።
በዘገባውም ሀገራችን በዓለም ዙሪያ በስፋት ከምትታወቅበት የቡና ምርት ባሻገር በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቱሪዝም እና በግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ውስጥ መግባቷን አስገንዝቧል።
ከ15 ዓመታት በፊት ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት የኢኮኖሚ አማካይ በታች የነበረችው ኢትዮጵያ፣ አሁን በአፍሪካ ውስጥ ካሉ 5 ግንባር ቀደም ኢኮኖሚዎች አንዷ እየሆነች መምጣቷ በአስደናቂ ዕድገት ተነስቷል። ዘገባው ይህንን ግዙፍ ሀገራዊ ግስጋሴ በዋና ዋና ምሰሶዎች ከፋፍሎ አቅርቦታል፦
የቀጣናው የኃይል ማዕከል - ታላቁ የህዳሴ ግድብ
ሙሉ በሙሉ ከ4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚገመት የኢትዮጵያውያን የገንዘብ አቅም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ወደ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ፈጥሯል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ለበርካታ ቤቶች ኃይል ከማቅረብ ባለፈ እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ እና ሱዳን ላሉ ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ በመሸጥ ኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ እያስቻላት ይገኛል።
በተጨማሪም በግድቡ ዙሪያ የተፈጠሩት 72 ደሴቶች በቀጣይ ትልቅ የቱሪስት መስህብ እንደሚሆኑ ዘገባው አብራርቷል።
የማዕድን ልዕለ-ኃያል የመሆን ራዕይ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የኩርሙክ የወርቅ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ መነቃቃት በተጨባጭ የሚያሳይ ነው። በካናዳው አላይድ ጎልድ ኮርፖሬሽን የሚመራው ይህ ፕሮጀክት፣ በዓመት 9 ቶን ወርቅ የማምረት አቅም አለው።
ከዚህም በላይ ወርቁን ወደ ውጭ ልኮ ከማቀነባበር ይልቅ በቦታው ላይ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ እየተገነባ መሆኑ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዕድገት አቅጣጫ የሚያሳይ ነው።
ግዙፉ የብሾፍት አውሮፕላን ማረፊያ
በ12.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው የበሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደግሞ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን በማስተናገድ አዲስ አበባን እንደ ዱባይ እና ዶሃ ያለ የአቪዬሽን እና የካርጎ ማዕከል ለማድረግ ያለመ ግዙፍ መሠረተ ልማት ነው።
ቱሪዝም
የኢትዮጵያን ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ማሻሻ አመላካች የሆነው ቱሪዝም ምን ያክል በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ በዝርዝር ተመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ 140 ሚሊዮን የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት እና 70 በመቶ የሚሆነው ከ30 ዓመት በታች የሆነ ወጣት አምራች ኃይል ያላት ኢትዮጵያ፣ ኢኮኖሚዋን በማስፋፋት ለራሷ የወደፊት ብልጽግና ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ቀጣና የኢኮኖሚ ሞተር እየሆነች መምጣቷን ዘገባው በሚገባ አሳይቷል ይላል ሲኤንኤን!
ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዥቅ እና ውስጣዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ከቀደመው የዕዳ ጥገኝነት ወጥቶ ወደ ተወዳዳሪነት እና ዘላቂ ዕድገት እየተሸጋገረ መሆኑን ዘገባው አብራርቷል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: