Search

የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአቪየሽን ዘርፍ መሪነቷን እንደታጠናክር ያስችላታል - ሲኤንኤን

ማክሰኞ ሐምሌ 28, 2018 48

የዓለማችን ታዋቂው የዜና መረብ ሲኤንኤን (CNN) "ኮኔክቲንግ አፍሪካ" በተሰኘው ዝነኛ ፕሮግራሙ፣ የአፍሪካ የአቪዬሽን መሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየመራው ያለውን ታላቅ የመሠረተ ልማት፣ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም እምርታ በሰፊው ዳስሷል።

ዘገባው እንደ አመላከተው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአህጉሪቱ ምሳሌ የሚሆን የዕድገት ሞተር ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ትስስር ማዕከል በማድረግ ረገድ ወደ አዲስ እየተሸጋገረ ይገኛል።

ዘገባው ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፏን ዘመናዊ በማድረግ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን (AfCFTA) ተግባራዊነት በማፋጠን እና የተፈጥሮ ሀብቶቿን ለዓለም አስተዋውቃ የቱሪዝም አቅሟን በመገንባት በኩል እያከናወነቻቸው ያሉትን ዐበይት ተግባራት በስፋት አሳይቷል።

በዘገባው ጎልተው ከተካተቱት ዐበይት ጉዳዮች መካከል 12.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው እና በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሜጋ ፕሮጀክት ቀዳሚው ነው።

ይህ ዘመናዊ የአቪዬሽን መንደር የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ እና 4 ሚሊዮን ቶን ካርጎ የማጓጓዝ ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከሲኤንኤን ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ አፍሪካውያንን እርስ በእርስ በማስተሳሰር ረገድ የመሪነት ሚናውን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በተጨማሪም አየር መንገዱ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን ስኬታማ ለማድረግ እና አህጉራዊ የንግድ ትስስርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁልፍ ሞተር መሆኑን አስረድተዋል።

በዘገባው ላይ እንደተጠቆመው የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብቶች ለዓለም አቀፍ እና ለአህጉራችን ጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የማረፊያ ስፍራዎች እና አዳዲስ የመንገድ ዝርጋታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ይህም ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።

የሲኤንኤን ዘገባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ዘርፍ እያመጣ ያለውን ብሩህ ተስፋ እና በአቪዬሽን መሠረተ ልማት አህጉራዊ መሪነቷን በጽኑ የምታረጋግጥበትን የልማት ጉዞ በግልጽ ያሳየ ነው።

የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀገራችን የአህጉሪቱ ዋና የንግድ፣ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ መገናኛ ማዕከል በማድረግ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: