ትናንት ሀገራችን ኢትዮጵያ በዝናብ እና በጭቃ ውስጥ ታላቁን የአረንጓዴ ዐሻራ ስታሳርፍ የዛፍ ተከላ ዘመቻ ማካሄዷ ብቻ አልነበረም።
ይልቁንም የመላውን ዓለም ቀልብ የሳበውን ትልቅ ሀገራዊ መመሪያዋን በተግባር እያረጋገጠች ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስተላለፉት "ያልናትን እስክንፈፅም ድረስ መድከም አይቻልም!" የሚለው ጥልቅ መልዕክት ዛሬ የኢትዮጵያ አዲሱ መታወቂያ እና የህልሟ ማሳኪያ ምልክት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በቃሏ የምትገኝ፣ የያዘችውን ዓላማ ሳታጠናቅቅ የማታቆም የጽናት ምድር መሆኗን በተግባር እያሳየች ነው።
ትናንት በአንድ ጀምበር የተተከሉት ሚሊዮን ችግኞች ዜጎች ያለምንም ቁሳዊ ጥቅም በበጎ ፈቃደኝነት ያፈሰሱት ወዝ እና እስከ ምሽት ድረስ የዘለቀው ተጋድሎ የሚያስረዳን አንድ ትልቅ እውነት አለ።
ይኸውም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሳታጠናቅቅ በግማሽ መንገድ ላይ የመተው ባህል የሌላት መሆኑን ነው።
ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአፈር መሸርሸርን ለመግታት የተዘረጋ ረጅም ዕይታ ያለው ሀገራዊ መሰረት ነው።
ቃል መግባት ቀላል ሊሆን ይችላል፤ በፈተናዎች እና በድካም መካከል አልፎ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ እና ውጤት ማሳየት ግን የኢትዮጵያውያን እውነተኛ መለያ ባሕሪ ነው።
ለዚህ የማይበገር የተግባር ጽናት ደግሞ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በላይ የተሻለ ሕያው ምስክር ሊኖር አይችልም።
ይህ ግዙፍ የትውልድ ፕሮጀክት ሲጀመር "አይቻልም" ያሉ፣ ኢትዮጵያ በገንዘብም ሆነ በቴክኖሎጂ ለማጠናቀቅ አቅም የላትም ብለው የደመደሙ በርካቶች ነበሩ።
ሀገራችን ግን የውጭ ጫናዎችን፣ የፋይናንስ እጥረቶችን እና ዘመናት የፈጀውን ፈተና ሁሉ አልፋ በገዛ ልጆቿ ላብ፣ ዕውቀት እና ቁርጠኝነት ግድቡን ገንብታ አጠናቅቃለች።
የሕዳሴው ግድብ ፍፃሜ ኢትዮጵያ "ያልናትን እስክንፈፅም አንደክምም" የሚለውን መርሆዋን ለዓለም ያስመሰከረችበት ታላቅ የድል ማሳያ ነው። የጀመረችውን ሳታጠናቅቅ እንደማታቆም ለወዳጅም ለጠላትም በተግባር ያሳየችበት የታሪክ ማህተም ነው።
በመሆኑም ከሕዳሴው ግድብ ማጠናቀቅ እስከ አረንጓዴ ዐሻራ ስኬት የተገነባው የተግባር ጽናት አሁን ለጀመርናቸው እና በቀጣይም ለምናሳካቸው የልማት ሥራዎች ሁሉ ትልቅ የሞራል እና የስኬት መነሻ ሆኖናል።
በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ሙሉ በሙሉ እስክናረጋግጥ፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ እና በመሠረተ ልማት የበለጸገች ሀገር እስክንገነባ፣ እንዲሁም የዜጎቻችንን ሕይወት በዘላቂነት የሚቀይሩ ታላላቅ ሀገራዊ ዕቅዶችን ዳር እስክናደርስ ድረስ የያዝነውን የልማት ጉዞ የሚያስቆመውም ሆነ የሚያስተጉለው ምድራዊ ኃይል አይኖርም።
ኢትዮጵያ አሁን ወደኋላ የማትመለስበት፣ የጀመረችውን ፕሮጀክት ሁሉ በድል የምታጠናቅቅበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች።
የነገዋ ኢትዮጵያ የዛሬ የጽናታችን ፍሬ ናት። "ያልናትን እስክንፈፅም ድረስ መድከም አይቻልም" የሚለው መሪ ቃል የትናንት ስኬታችንን ብቻ ሳይሆን፣ የነገውን ሀገራዊ ከፍታችንን የሚወስን የሕይወት መመሪያችን ነው።
ፈተናዎች ሊበዙ፣ መንገዶች ሊጠብቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነትና በኅብረት ሲቆም የማይሻገረው ተራራ እንደሌለ በታሪክ ያስመሰከረው እውነት ነው።
የጀመርነውን ሳንጨርስ አናርፍም፤ ያልናትን ሳንፈፅም አንደክምም። የበለጸገች፣ የተከበረች እና በመሰረቶቿ ላይ በራሷ እግር የቆመች ኢትዮጵያ እውን የምትሆነው በዚህ የማይበገር የታታሪነት እና የጽናት ወኔ ብቻ ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: