በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥይት አፈሙዝን በውይይት ጠረጴዛ፣ የጦር ሜዳ ጀግንነትን ደግሞ በሐሳብ ልዕልና ለመተካት የሚያስችል እጅግ ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
"እስኪ ዝም እንበልና እንደማመጥ፤ ኢትዮጵያ ምን እየገጠማት ነው?" ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ፣ ለዘመናት "እኔ ከሞትኩ፣ አንተ አትኖርም" በሚል የዜሮ ድምር ፖለቲካ ስንተራመስ፤ ከደም፣ ከእንባ እና ከውድመት ውጪ ያተረፍነው አንዳችም ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን።
ኢትዮጵያ በታሪካዊ እና መዋቅራዊ ስብራቶች ውስጥ በማለፍ፣ የትናንት ቁስል በዝምታ ሸፍኖ ነገን በጉልበት ለመቅረጽ የተደረጉ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እጅግ ከባድ ዋጋ አስከፍለውናል። አሁን ግን "እኔ" የሚለው ትርክት አብቅቶ "እኛ ማን ነን?" የሚለውን የወል እውነታ የምንመልስበት እና "አንተም አሸናፊ፣ እኔም አሸናፊ" የሚል ማንም በማይደማበት የጠረጴዛ ላይ ጦርነት ሀገርን የማትረፍ አዲስ የፖለቲካ ሂሳብ እየሰራን እንገኛለን።
በግጭት አፈታት እና የሰላም ግንባታ ጥናቶች በተለይም እንደ ጆን ፖል ሌደራች ያሉ የዘርፉ ምሁራን እንደሚያስረዱት፣ መዋቅራዊ እና ጥልቅ ታሪካዊ ስብራት ያለባቸው ማኅበረሰቦች ዘላቂ ሰላም ሊያመጡ የሚችሉት አካታች የውይይት መዋቅሮችን መገንባት ሲችሉ ብቻ ነው።
የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚዎችም ቢሆኑ በድህረ-ግጭት ሀገረ-መንግሥት ግንባታ (Post-conflict State-building) ሂደት ውስጥ እውነተኛው ድል የሚገኘው በጦር ሜዳ ሳይሆን፣ ጠብመንጃን በማስቀመጥ በሚደረግ የጠረጴዛ ላይ ድርድር መሆኑን ይስማሙበታል።
ከእንግዲህ በጠብመንጃ አፈሙዝ የሚፈታ የፖለቲካ እዳ፣ የሚገነባም አዲስ ሀገር አይኖርም። የዓለማችን የበለጸጉ ሀገራት ተሞክሮ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት የሚገነባው በሰጥቶ መቀበል መርህ እንጂ በአንድ ወገን የሐሳብ የበላይነት አይደለም።
ይህንን ሳይንሳዊ እና ተግባራዊ እውነታ ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስናመጣው፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደታችን አሁን የደረሰበት ምዕራፍ እጅግ ተስፋ ሰጪ ሆኖ እናገኘዋለን። ሂደቱ የዝግጅትና የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፎችን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቆ፣ በአሁኑ ሰዓት ጉባኤው ተሰብስቦ በዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በቀጥታ እየመከረ እና እየተወያየ ይገኛል።
ከጫፍ እስከ ጫፍ የተሰባሰቡ፣ የተለያየ የፖለቲካ፣ የእምነት እና የማንነት አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሕዝብ ብሶቶችን፣ የዘመናት እሮሮዎችንና ተስፋዎችን ወደ መፍትሄ እየቀየሩ ነው። ይህ ምክክር ምዕራፍ የሚያሳየን ትልቁ ስኬት፣ "የእኔ ሐሳብ ብቻ ይበልጣል" ከሚለው የትናንት አግላይ አባዜ ወጥተን፣ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ መንገድ ወደምናስተናግድበት የጋራ ማዕቀፍ መሸጋገራችንን ነው።
በዚህ የምክክር ጉባኤ ላይ ሐሳቦች ይጋጫሉ፣ ይፋጫሉ፤ ነገር ግን በልዩነት መዋደድ እና የሐሳብ ፍጭት ሀገርን እንዴት እንደሚያፀና በተግባር እየታየ ነው። በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የሐሳብ ልዩነቶች በጠረጴዛ ላይ በሰላማዊ መንገድ መቅረባቸው የጥፋት ሳይሆን፣ የብልጽግና እና የውበት ምንጭ ናቸው።
አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አሸናፊና ተሸናፊ የሚለይበት የፍርድ አደባባይ ሳይሆን፣ ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበትን የጋራ መንገድ የምንቀይስበት ነው። ይህ ጉባኤ የማንነትን እስር ቤት የሰበረ፣ "የማንም ያልሆነችውን ግን ደግሞ የሁላችንም የሆነችውን" ሀገር በአዲስ መልክ እያዋለደ የሚገኝ ታሪካዊ ክስተት ነው።
ይህ ታሪካዊ የምክክር ጉባኤ የተወሰኑ የፖለቲካ ልሂቃን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሁላችንም የኅልውና ጉዳይ ነው። ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው እያካሄደ ያለውን ወሳኝ የአጀንዳዎች ምክክር ዳር ለማድረስ፤ ወጣቱ የነገዋን ሀገር የሚረከብበትን መሠረት የሚጥልበት፣ ምሁራንና የሲቪክ ማኅበራት ዕውቀታቸውን ለጋራ መግባባት የሚያውሉበት፣ ዲያስፖራው በያለበት ሆኖ የሰላም ግንባታውን የሚደግፍበት ጊዜ አሁን ነው።
የፖለቲካ ባህላችን ከጠላትነት ወደ ተፎካካሪነት፣ ከሴራ ወደ ግልጽነት እያደገ መምጣቱ ቀጣይ ለሚኖረው ሀገራዊ መረጋጋት ትልቅ ፋይዳ አለው። ቂምና ቁርሾን ለትናንት ትተን ክፉ ታሪካችንን በሰላም ስንቀብረው እንዲሁም ጦር ያነሱ የሰላም ካርድ ተጠቅመው ጠብመንጃቸውን ስያስቀምጡ፣ አሸናፊው መላው ሕዝብ እና ሀገር ይሆናል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: