Search

እንደ ሕዝብ ችለናል፤ እንደ ሀገር ጀግነናል!

ረቡዕ ሐምሌ 29, 2018 38

በአንድ ጀንበር 805.3 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ያስመዘገብነው የአረንጓዴ ዐሻራ ውጤት፣ በየትኛውም ዓለም አቀፍ ሚዛን ሲሰፈር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ታላቅ ስኬት የዘመናችን ዳግማዊ የዓድዋ ድል ነው። በየአካባቢው፣ በየሰፈሩ፣ በየተራራው እና በየሸንተረሩ እየተዘራ ያለው ችግኝ ብቻ ሳይሆን፣ አዲስ አረንጓዴ ህይወት ነው።

ዓለምን እያነጋገረ እና እያስደነቀ ያለው ይህ የአንድ ጀንበር ገድል፣ በርካታ ያደጉ ሀገራት በድምር እንኳ ሊያሳኩት ያልቻሉት፣ ኢትዮጵያውያን በመተባበር የፈጸሙት ታሪካዊ ክስተት ነው። እንደ ሕዝብ ተባብረን ከሠራን የማይቻል ነገር እንደሌለ በተግባር ያረጋገጥንበት ደማቅ ማሳያ ነው።

ጥቂቶች ጥግ ይዘው በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ላይ ሊያፌዙ ቢሞክሩም፣ ተፈጥሮ ግን በተግባር ዝምታን በሰበረ መንገድ ምላሹን እየሰጠቻቸው ትገኛለች። በተከልነው አረንጓዴ ዐሻራ ተፈጥሮ እየታከመች፣ ኢትዮጵያችን ከድርቅና ከበረሃማነት እያገገመች እንዲሁም መልሳ ህይወት እየዘራች ነው። ዛሬ አፈርን እየቆፈሩ እጃቸው በጭቃ የተለወሰ ዜጎች፣ ለነገው ትውልድ እና ለልጆቻቸው የሚበላውን እና የሚመገበውን ጸጋ ነው እያረጋገጡ ያሉት። እየተተከለ ያለው ዛፍ ብቻ ሳይሆን፣ የተስፋ ብርሃን እና የነገዋ የበለጸገች ሀገር መሠረት ነው።

እየተተከለ ያለው አረንጓዴ ህይወት፣ የነገው ማክሮ ኢኮኖሚ ዋነኛ የጀርባ አጥንትም ጭምር ነው። በክረምት ዝናብ የታጠበው እና የተራቆተው አፈራችን እየተጠበቀ፣ የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንዲሁም የከርሰ ምድርም ሆነ የገጸ ምድር የውሃ ሀብታችን ዘላቂ በሆነ መንገድ ጥበቃ (Preservation) እየተደረገለት ይገኛል። እያንዳንዷ በላብ ጠብታ የተተከለች ችግኝ ስትደመር ነገ ግዙፍ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ታመጣለች።

ዛሬ የምንተክላት ችግኝ የነገ የውሃ ጥበቃ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የካርበን ልቀትን የመቀነስ አቅም እና በምግብ ራስን የመቻል ዋስትና ናት። በአጠቃላይ ነገ በማክሮ ደረጃ ታላቅ ተአምር ሆኖ ይፈጠራል። ሌላው ቢቀር ይህ ዓይነቱ ግዙፍ ሀገራዊ ንቅናቄ፣ እንደ መንግሥት ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ እና ፖሊሲ ተደርጎ መያዙ በራሱ እጅግ ሊደነቅ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በርካታ መንግሥታት እና ሀገራት በዚህ ደረጃ፣ በዚህ ልክ እና በዚህ መሠረት የሕዝብን ንቅናቄ በመፍጠር በከፍተኛ ቁርጠኝነት አረንጓዴ ልማትን ማሳካት ተስኗቸዋል። የእኛ ሀገር የፖሊሲ ትኩረት ግን ይህንን ተአምራዊ ንቅናቄ ወደ መሬት አውርዶ እውን አድርጎታል።

ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ካደረጓቸው ታላላቅ ሀገራዊ ንቅናቄዎች ውስጥ አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው። አረንጓዴ ዐሻራችን አዲሱ ዳግማዊ ዓድዋችን ሆኖ ዛሬ ላይ በኩራት እየተወለደ ነው። ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር ታላቅ እርምጃ አቅልለን ልናየው አይገባም። እንደ ሕዝብ አንድነታችንን አጠናክረን ችለናል፣ እንደ ሀገር ደግሞ ጀግንነታችንን በተግባር ያረጋገጥንበት ህያው የታሪክ ማህደር ነውና!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: