Search

የበጎ ፈቃደኝነት ባህል፡- የዜጎች ሕይወት መታደስና የማህበራዊ ክብር ከፍታ

ረቡዕ ሐምሌ 29, 2018 41

የክረምት ወራት ሲመጣ የሰማይ መስኮቶች ሲከፈቱ ታላቅ ተስፋን የሚፈነጥቀውን ያህል፣ በተጎሳቆሉ ጎጆዎች ውስጥ ለሚኖሩ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ግን የዝናብ ጠብታዎች የስጋትና የጭንቀት ምንጭ ሲሆኑ ይስተዋላል።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ከቤቶች እድሳት መርሐግብር ጋር ተያይዞ የተጀመረው የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን የመታደስና የክብር ሕይወት እውን በማድረግ ላይ ይገኛል።

መርሐግብሩ በዋናነት የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን ማጠናከር፣ ማህበራዊ አንድነትን ማጎልበት እና ዜጎች እውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የማህበረሰባቸውን ችግሮች ለመፍታት እንዲያውሉ ማበረታታትን ዓላማ ያደረገ ነው።

በየዓመቱ ትምህርት ቤቶች ለእረፍት ሲዘጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ከተሞች ያሉ ሰፈሮችን ገጽታ በትብብር ይለውጣሉ።

ወጣቶቹ ዝናብ የሚያስገቡ ያረጁ ቆርቆሮዎችን በመተካት፣ የተናዱ ግድግዳዎችን በማጠናከርና የፍሳሽ መስመሮችን በመቆፈር አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ወደ ተሟላ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ።

ከቤቶች እድሳት ባሻገር፣ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ በመትከል፣ በሕክምና አገልግሎትና የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን በማሻሻል ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

ያለምንም የገንዘብ ክፍያ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተው ይህ አገልግሎት የማህበረሰብ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ በወጣቶችና በአረጋውያን መካከል ጥልቅ ፍቅርና ትስስርን ይፈጥራል።

ወጣቶቹ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ሲሰጡ፣ አረጋውያኑ ደግሞ ምርቃታቸውን፣ ምክራቸውንና ደስታቸውን ያካፍላሉ።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ ጥገኝነት ተላቃ በራስ አቅም የመደጋገፍ ባህልን በማጠናከር ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተለመደው የበጎ አድራጎት ስራዎች ባለፈ ለሀገር ግንባታ የሚውል የሀገራዊ ንቅናቄ ወቅት ሆኗል።

ይህ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ዜጎች ተረጂ ከመሆን ተላቀው የጋራ አቅማቸውን በማቀናጀት ለዘላቂ ልማት እንዲሰሩ የሚያነሳሳና ኢትዮጵያዊነትን በተግባር የምናሳይበት የጋራ ጉዞ ነው።

መርሐግብሩ በኢኮኖሚ በኩል የበጎ ፈቃደኞችን አስተዋጽኦ በማስተባበር የመንግሥት ተቋማትን የገንዘብ ጫና የመቀነስና ለልማት ፕሮጀክቶች አቅም የመሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

በማህበራዊ በኩል ደግሞ በተለያዩ ክልሎችና ባህሎች መካከል ትብብርን ያጎለብታል። በአጠቃላይ የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቁ የዜግነት ተሳትፎንና ሀገራዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ የባህል ግንባታ ሚና እያበረከተ ይገኛል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: