Search

የባሕር ዳር ከተማን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡- የከተማዋ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ

ሰኞ ነሐሴ 12, 2017 86

የባሕር ዳር ከተማን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚያሻሽሉ እና የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ገልጿል፡፡
ከተማዋ ቀድሞ የነበረው የቱሪስት እንቅስቃሴዋ እንዲመለስ ብሎም እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ ጋሻው እንዳለው በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡
ቱሪዝም የሀገርን ታሪክ የማስተላለፍ፣ አንድነትን የመግመድ አቅም እንዳለው አንስተው፤ ይህን የሚያጠናክሩ የባሕል ፌስቲቫሎች፣ የቁንጅና ውድድር እና መሰል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡
አስጎብኚ ድርጅቶች እና ሆቴሎች ጎብኚዎችን በተገቢው መልኩ እንዲያስተናግዱ በማድረግ ጥሩ የቆይታ ግዜ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ትኩረት የተነፈገውን የኪነ ጥበብ ስራን በፓሊሲ አካቶ መስራት መቻሉን አስታውሰው፤ በከተማዋ ያሉ መዳረሻዎችን ምቹ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ጥገና የሚፈልጉ ቅርሶችን መጠገን እና ለትውልድ ጠብቆ ለማቆየት እንቅስቃሴ መጀመሩን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገልፀዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማው ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የተግባር አፈፃፀም የእውቅና እና የ2018 የእቅድ ትውውቅ መድረክ ላይ ነው ይህን የተናገሩት፡፡
ለዚህም ከባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ለፈጸሙ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ባለድርሻ አጋሮች እውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት መሰጠቱ ተገልጿል፡፡
በአፎሚያ ክበበው