ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነውን የመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ማሻሻያ ተከትሎ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በሚፈፅሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ማሻሻያው ከሀገራችን ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ከ2% የማይበልጠውን የመንግስት ሠራተኛ የኑሮ ሁኔታ ለማገዝ ብሎም መንግስት ለሕብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በማሰብ የተላለፈ መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ወንዱሙ ፍላቴ ገልፀዋል፡፡
ሆኖም በንግድ ስርዓቱ ውስጥ በሚያስመሰግን ተግባር የሚሳተፉ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በአፍቅሮተ-ነዋይ የታወሩ ነጋዴዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሯሯጡ መስተዋላቸውን ለኢቢሲዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ፣ ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍጠር ምርት የሚሰውሩ እና አላግባብ የሚያከማቹ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች በአዋጅ ቁጥር 980/2008 እና 813/2006 ፤ እንዲሁም በወንጀል ሕግ 1996 ስር ተጠያቂ እንደሚሆኑ በመጠቆም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
አስፈፃሚው አክለውም በየደረጃው የሚገኝ የንግድ መዋቅር ከሚመለከታቸው የፍትህ እና ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የገበያ ማረጋጋት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ የግብይት ሂደቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
በአፎምያ ክበበው