Search

የደመወዝ ጭማሪው ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞችን ያካትታል - የገንዘብ ሚኒስቴር

ሰኞ ነሐሴ 12, 2017 228

 

የደመወዝ  ጭማሪው  ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞችን ያካተተ ነው ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግሥት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ መንግሥት ከመስከረም ወር ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪ  ለማድረግ መወሰኑን ጠቅሰው፤ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደዚህ ያለ ጭማሪ መደረጉ መንግሥት የቋሚ የደመወዝ ተከፋዮችን የኑሮ ጫና ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የደመወዝ  ጭማሪው 160 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት የተበጀተለት እንደሆነም አንስተዋል።

ጭማሪው የዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋዮችን ጫና ውስጥ እንዳይከት የታለመ ነው እንደሆነም ነው ነው የጠቀሱት።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤የመንግሥት ሠራተኛው የበለጠ አምራች እንዲሆን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ኑሮውን በአግባቡ የሚመራበት ገቢ ሊያገኝ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህም መንግሥት ባለፈው በጀት ዓመት የደመወዝ  ጭማሪ ማድረጉን አስታውሰው፤ይህ ጭማሪ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ ባለመሆኑ  በሳይንሳዊ ዘዴ ተጠንቶ የደመወዝ  ጭማሪ እንዲደረግ ተወስኗል ብለዋል።

የመንግሥት ሠራተኛው ሥራውን  በስነ- ምግባር እና በውጤታማነት መፈጸም እንደሚገባውም ጠቅሰዋል።

መንግሥት ሠራተኛው መካከለኛ ገቢ ላይ እስኪደርስ ማሻሻያው የሚቀጥል መሆኑንም ነው ኮሚሽነር የተናገሩት።
በሜሮን ንብረት