Search

በኢትዮጵያ ለቱሪዝም በተሰጠው ትኩረት ውጤት እየተገኘ ነው፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሰኞ ነሐሴ 12, 2017 81

በኢትዮጵያ ለቱሪዝም በተሰጠው ትኩረት ውጤት እየተገኘ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት፣ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ ሁለተኛው የካሪቢያን እና አፍሪካ መሪዎች “ካሪኮም” ጉባኤን አስመልክቶ ከሆቴል ኢንዱስትሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመጭው ጳጉሜን እና መስከረም ወር ኢትዮጵያ ለምታስተናግዳቸው ጉባኤዎች ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን በአዲስ አበባ የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኃላፊዎች እና ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ ለቱሪዝም በተሰጠው ትኩረት ውጤት እየተገኘ መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገልፀዋል።
ለአብነት በ2017 በጀት ዓመት ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ143 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መሆኑን ነው ከንቲባ አዳነች የጠቀሱት።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአየር ንብረት ጉባዔው የሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
እስካሁንም 14 ሺህ ሰዎች መመዝገባቸውን የገለፁት ዶ/ር ፍፁም፤ ጉባዔው ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ያከናወነቻቸውን ተግባራት የሚያጎላ እንደሆነ ገልፀዋል።
በጉባዔው የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ የሚያስተዋወቁ የቱሪዝም መስህቦችን የሚያሳዩ አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ናቸው።
ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ከጉባዔው ባሻገር ዘላቂ የቱሪዝም ትስስር በማሰብ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ ተመጣጣኝ ዋጋ ማድረግ እና ሀገራዊ ገፅታን መገንባት ላይ ተኩረት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለቱሪዝሙ በመንግስት የተሰጠውን ትኩረት አድንቀው፤ ለመጪዎቹ ጉባዔዎችም ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንና ገልፀዋል።
በሞላ ዓለማየሁ