መንግሥት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና የተፈናቀሉትን ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ የሰላም በሩን ክፍት አድርጎ ሰፊ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በተለይም በፕሪቶሪያው ስምምነት የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና በጦርነት ሳቢያ የደረሰውን ዘርፈ ብዙ ውድመት ለመጠገን ጉዳዩን በትዕግሥት በመያዝ ለሰላም ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ ነው።
ይሁን እንጂ ይህ የሰላም አማራጭ በሰፊው እየቀረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ከግጭትና ከትርምስ ውጭ መኖር የማይችልበትን እኩይ ማንነቱን በድጋሚ እያሳየ ይገኛል።
ቡድኑ ሰላምና መረጋጋት ሲሰፍን የፖለቲካ ህልውናው የሚያከትም ስለሚመስለው፣ ሁሌም ቢሆን ጭር ሲል የማይወድ፣ ጠብ አጫሪና የችግር ጠንሳሽ ነው።
"ስልጣኑን በበላይነት ተቆጣጥሬ የህዝብ ሀብት ካልዘረፍኩ ሀገር ትፍረስ" የሚል ፅንፈኛ አቋሙን መተው ያቃተው ይህ ህገ-ወጥ ስብስብ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተመሰረተውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በመገረሰስና ኢ-ህገመንግሥታዊ ሥርዓት በመዘርጋት ክልሉን በሥርዓተ አልበኝነት ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ይህ ቡድን ሰላም የህልውናው ማክተሚያ እንደሆነ አጥብቆ ስለሚያምን፣ እሱ በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ የጥላቻ ንግግሮችን እና የትርምስ አጀንዳዎችን በስፋት ማሰራጨቱን ቀጥሏል።
ከዚህም አልፎ የሰላም ጠላት ከሆኑ የተለያዩ ሃይሎች ጋር ህገ ወጥ ጥምረት በመፍጠር የእሱን የፅንፈኝነት አጀንዳ ለማስፈጸምና ቀጠናውን ለማተራመስ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።
ቀደም ሲል በጫረው አውዳሚ ግጭት ሳቢያ ወጣቶችን ለከንቱ የፖለቲካ ፍላጎቱ በመገበር ክልሉን ያለ ወጣት ለማስቀረት መኳተኑና በርካታ እናቶችን ለከፍተኛ የሥነ ልቦና እና የህይወት ስብራት መዳረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የትግራይ ህዝብ ደህንነትና ልማት ከቶውንም እንደማያሳስበውና ህዝቡን ለእኩይ የፖለቲካ ፍላጎቱ ማስፈጸሚያ ዋሻና መያዣ አድርጎ የሚጠቀምበት መሆኑ የቡድኑ የማይለወጥ ማንነት ነው።
ሆኖም ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿን የተቀናጀ ሴራ በጣጥሳ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቅ የቻለች ጠንካራ ሀገር በመሆኗ፣ አሁንም ህገ-ወጡንና ጠብ አጫሪውን ኃይል በጥቁር ታሪኩ ትታ፣ መንግሥት ከተባበረውና ከጠንካራው የሕዝቧ ክንድ ጋር በመሆን የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበር፣ የሰላምና የልማት ግቦችን ከዳር የማድረስ ዝግጁነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: