ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የያዙት የትጥቅ ትግል በጫካ ውስጥ ተደብቆ ንፁሃንን ከመግደል እና ከመዝረፍ የዘለለ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ግብ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ጦርነት እና ግጭት አውዳሚ መሆናቸውን በመገንዘብ በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ መርጠው ወደ ኅብረተሰቡ እየተቀላቀሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት አሁንም ያልተለወጠ መሆኑን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማንኛውም አካል በሰላማዊ መንገድ ሀሳቡን ይዞ ለመታገል እስከፈለገ ድረስ የመንግሥት የሰላም በር መቼም ቢሆን እንደማይዘጋ አስገንዝበዋል።
የኦሮሞን ሕዝብ ትግል በዋናነት የጀመሩ እና ያደራጁ አንጋፋ ፖለቲከኞች በአሁኑ ወቅት ሀገር ቤት ገብተው በፓርላማ እና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ በሰላም እየተሳተፉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በአንፃሩም፣ አሁን የትጥቅ ትግሉን ከሚመሩት አካላት ጀርባ ያለውን ተቃርኖ አንስተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ላይ በጫካ ውስጥ የሚገኙት ኃይሎች የማንን አጀንዳ እያስፈፀሙ እንደሆነ ሕዝቡና ወጣቱ ቆም ብሎ ሊጠይቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጠመንጃ ኃይል ሊገነባ እንደማይችል ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ብልፅግና ፓርቲ በብቁ ሀሳብ እና በአሸናፊ ፖለቲካ ላይ የተመሠረተ እንጂ በዘር ላይ የተንጠለጠለ አደረጃጀት አለመሆኑን አብራርተዋል።
የትኛውም የፖለቲካ ቡድን ፍላጎቱን ማሳካት የሚችለው ሕዝብን አሳምኖ በምርጫ ሲያሸንፍ ብቻ መሆኑን በአፅንዖት ተናግረዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: