ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በሀገራችን ብሎም በኦሮሚያ ክልል ለሚታየው የጸጥታ ችግር መሠረታዊ ምክንያቶችን በዝርዝር አብራርተዋል።
ለችግሮቹ ዋና ዋና ምክንያቶች ያሏቸውም የፖለቲካ ሽግግሩ ተፈጥሯዊ ፀባይ፣ የሥልጣን ማዕከል ሽግግር እና የትጥቅ ኃይሎች መዳከምን ተከትሎ የተፈጠረ ያልተጠበቀ ጥምረት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የሥልጣን ማዕከል ሽግግሩን እና የፖለቲካውን ተፈጥሯዊ ፀባይ በተመለከተ ሲያብራሩ ቀድሞ ኢትዮጵያን በብቸኝነት ሲመራ የነበረው ቡድን ሥርዓቱ ሁሉንም አሳታፊ ወደሆነ መንገድ መግባቱን ባለመቀበል ሥልጣን በጉልበት ለመመለስ እያደረገ ያለው ጥረት ለግጭቶች መንስኤ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብዙ እምነቶች፣ ቋንቋዎች እና ባህሎች ባለቤት በመሆኗ በአንድ ብሔር ወይም ቡድን የበላይነት ብቻ ልትመራ እንደማትችልም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የትጥቅ ኃይሎች መዳከምን ተከትሎ ስለተፈጠረው ያልተጠበቀ ጥምረት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች መንግሥትን ማሸነፍ እንደማይችሉ ሲገነዘቡ ያልተቀደሰ ጋብቻ መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ትናንት አንዱን ከሌላው ጥቃት እንዲታደጓቸው መንግሥትን ሲወተውቱ የነበሩ ኃይሎች፣ ዛሬ ተጣምረው መሰለፋቸው ምን ያህል እንደተዳከሙ እና ተስፋ እንደቆረጡ የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም አልፎ እነዚህ ኃይሎች እንደ ኤርትራ እና ሱዳን ያሉ የውጭ አካላትን ለእርዳታ እየጋበዙ መሆኑን ሕዝቡ ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ይህንን የተዛባ ትርክት በማረም እንዲሁም አፍራሽ ከሆነ አስተሳሰብ በመውጣት፣ ሁሉንም የሚያስታርቅ እና የተሻለ ሀሳብ የሚያመጣ ውህድ መንገድ መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: