ጊዜ ወደ ፊት የሚነጉድ፣ ዘመን የማይቆም ተፈጥሯዊ ሀቅ ቢሆንም እንደ ሕገ-ወጡ ህወሓት ያሉት ግን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ከተተከሉበት ጠባብ ርዕዮተ-ዓለም አጥር መውጣት አቅቷቸው የታሪክ ዕዳ ሆነው ይኖራሉ።
በ1967 ዓ.ም የደደቢት በረሃ ሲረግጡ የነበረውን የብሔር ፖለቲካ ቅስቀሳ፣ የማኦ ዜዶንግ የረጅም ጊዜ የገበሬዎች የሽምቅ ውጊያ ስልት እና የውጭ ጠላቶችን ተገን የማድረግ ባሕሪ ዛሬም ድረስ አጽንተው የያዙት የሕገ-ወጡ ህወሓት አመራሮች፣ የፖለቲካ ሰዓታቸው በዚያው በ1967 ዓ.ም እንደቆመ ይገኛል።
ቡድኑ የዛሬ 50 ዓመት በነበረበት ግትር አስተሳሰብ ላይ ተቸንክሮ በመቅረቱ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እውነታዎች መረዳት አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎም በቆመበት የቀረውን ስልት ተጠቅሞ በተመሳሳይ መንገድ አራት ኪሎ መግባት ይቻላል የሚል አደገኛ እና አጥፊ የፖለቲካ ስሌት ውስጥ ወድቋል።
ይህ የቆየ የክህደት እና የቅዥት ስሌት ዋና ማሳያው ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት ነበር። ለዘመናት የትግራይን ሕዝብ ከማንኛውም ስጋት ሲጠብቅ የኖረውን፣ አብሮት ማኅበራዊ ሕይወት መስርቶ ያረሰውን እና የቆረሰውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጀርባ በመውጋት የኖረበትን ሰይጠናዊ ምግባሩን ገለጠ።
የቡድኑ ልሳናት በወቅቱ በኩራት እንደገለጹት "መብረቃዊ የቅድመ-ተከላካይ ጥቃት" በማካሄድ የመንግሥትን ወታደራዊ አቅም በማዳከም አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ዝተው የነበረ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን የቡድኑ ወታደራዊ አደረጃጀት በትኖ ወደ 1967ቱ ደደቢት መመለስ ነበረ።
ከውድቀቱ የማይማረው ይህ ቡድን ሃምሳ ዓመት ወደ ኋላ የመለሰውን ሽንፈቱን ለመሸፈን ሲል ያወጀው ጊዜ ያለፈበት የ"ሕዝብ ማዕበል" ስልት የትግራይን ወጣት እንደ ቅጠል በማርገፍ የአጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎችን የጥፋት ቀጣና አደረገ።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አጣሪዎች እንደተረጋገጠው በዚህ የቡድኑ እብደት ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በውጊያ፣ በረሃብ እና በጤና መዋቅሮች መፍረስ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይህም ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ህልውና ሳይሆን ለራሱ ጠባብ የሥልጣን ጥም ሲል የአንድን ትውልድ ሕይወት የገበረ ራስ ወዳድ መሆኑን የሚያረጋግጥ ቁልጭ ያለ ታሪካዊ ማስረጃ ነው።
ከዚህ ሁሉ ዕልቂት ባሻገር ቡድኑን ከደደቢት በረሃ ጀምሮ ሲያንገላታው የኖረው ሌላው ፖለቲካዊ በሽታ የትግል ጓዶችን የመብላት ሴራ ነው። ህወሓት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የተለየ ሀሳብ ያመነጩትን በማጥፋት የራሱን አባላት እርስ በእርስ በማጋጨት እና የሥልጣን ጥሙን ለማርካት ሲል የገዛ ጓዶቹን መሥዋዕት በማድረግ ይታወቃል።
ዛሬም ቢሆን ይኸው የ50 ዓመት የሴራ ፖለቲካ አገርሽቶበት አመራሮቹ በመከፋፈል እርስ በእርስ እየተባሉ ይገኛሉ። ይህ የውስጥ ሽኩቻ እና የመጠፋፋት አባዜ ቡድኑ መቼም ቢሆን ከ1967ቱ የጠባብነት አረንቋ መውጣት እንደማይችል በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላም ቢሆን የሕገወጡ ህወሓት ቡድን የፖለቲካ ሰዓት መራመድ አልቻለም። ዛሬም ቢሆን የትግራይን ወጣት ከትምህርት እና ከሥራ ገበታው ነጥሎ በግዳጅ ወደ ውትድርና የማፈስ ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል።
የዓይን እማኞች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዳረጋገጡት፣ ቡድኑ ወጣቶችን በኃይል እያገተ ለሌላ የደም እልቂት ሲያዘጋጃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ደግሞ ከዚህ ደም መጣጭ ቡድን ለማምለጥ ሲሉ አካባቢያቸውን ጥለው እየተሰደዱ ነው።
ቡድኑ ወጣቱን ለሱዳን፣ ለግብፅ እና ለሌሎች የውጭ ኃይሎች ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መፈጸሚያ በመሸጥ እና የእነዚህ አካላት "ፈረስ" በመሆን ማዕከላዊ መንግሥቱን ለማዳከም የሚያደርገው መፍጨርጨር የቆየውን ጥመታዊ ስልቱን ያንጸባርቃል።
የሕገ-ወጡ ህወሓት ቡድን የትግራይን አዲስ ትውልድ ለራሱ የሥልጣን ቁማር ማገዶ በማድረግ የቀጣናውን ጠላቶች ደጅ በማጥናት፣ ጓዶቹን በመብላት እና በ1967 ዓ.ም አስተሳሰብ በመመራት አራት ኪሎን ዳግም ማለም አይችልም።
የትግራይ ሕዝብም ሆነ የመላው ኢትዮጵያ ወጣቶች የዚህን ቡድን የጥፋት መረብ እና በትግራይ ሕዝብ ስም የመነገድ የፖለቲካ ቁማር በሚገባ ተረድተውታል።
የቆመ ሰዓት ይዞ የዘመኑን ጉዞ ለመምራት መሞከር የጅልነት ቁንጮ ነው፡፡ ህወሓትም ከታሪክ ትምህርት ሳይወስድ በወጣቶች ደም ለመነጋገድ የሚያደርገው የመጨረሻ መፍጨርጨር በታሪክ መዝገብ ላይ በውርደት የሚደመደም ይሆናል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: