Search

የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን የማዳከም እና የመበተን ፍላጎት ላላቸው የውጭ ጠላቶች መሳሪያ በመሆን እያገለገለ ይገኛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ነሐሴ 02, 2018 108

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ስለመጣሱ ተናግረዋል።

የህወሓት ቡድን ዳግም ለጦርነት እያደረገው ስላለው ዝግጅት በሰጡት አስተያየት፣ ቡድኑ አሁንም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው አሮጌ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ እሳቤ እና አመራር ውስጥ ተቀርቅሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቡድኑ 27 ዓመታት ሀገርን አስተዳድሮ ከወረደ በኋላም ራሱን እንደ ነጻ አውጪ ግንባር በመቁጠር የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የራሱን ጠባብ የቡድን ፍላጎት ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህም ባለፈ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ታጣቂዎችን እንደ እኩል አጋር ሳይሆን እንደ መጠቀሚያ መሣሪያ በማድረግ ሀገርን የማፍረስ ዓላማ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ እንደሚገኝ እና ፌደራል መንግሥትም ይሁን ሌላ አካል አንድም ሜትር መሬትም ሆነ ሀብት እንዳልወሰደበት ገልጸዋል።

ይህም የቡድኑ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት እውነተኛ የሕዝብ ጥያቄን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን እንደሚያሳይ አስምረውበታል።

ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የማዳከም እና የመበተን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ፍላጎት ላላቸው ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች መሳሪያ በመሆን እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።

ቡድኑ 1980ዎቹ መጨረሻ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን አግልሎ ሥልጣን እንደያዘበት ዓይነት አካሄድ በአሁኑ ወቅት በፍጹም ሊሠራ እንደማይችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አሁን ያሉበት የፖለቲካ ንቃት እና ተሳትፎ ከትናንቱ በእጅጉ የተለየ መሆኑንም ተናግረዋል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: