ከ20 ዓመታት በፊት በናፍጣ መኪና የዓለም የመሬት ላይ ፍጥነት ሪከርድን ሰብሮ ማንም እንዳይነካው አድርጎ የቆየው ታዋቂው ብሪታንያዊ አሽከርካሪ አንዲ ግሪን፣ አሁን ደግሞ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ብቅ ብሏል።
የድምፅን ፍጥነት በመኪና በመስበር በዓለማችን ብቸኛው ሰው የሆነው ይህ የቀድሞ የሮያል አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪ፣ በዚህ ሳምንት በአሜሪካ ዩታ ግዛት በሚገኘው ታዋቂው የቦኔቪል የጨው ሜዳ ላይ በሃይድሮጅን ኃይል በሚሰራ መኪና አዲስ የፍጥነት ሙከራ ሊያደርግ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል።
አንዲ ግሪን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በናፍጣ ኃይል በሚሰራ መኪና በሰዓት 563.4 ኪሎ ሜትር ፍጥነት በመድረስ የዓለምን የመሬት ፍጥነት ሪከርድ ማስመዝገቡ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ "የወደፊቱ ነዳጅ" ብሎ የሚጠራውን ንጹህ የሃይድሮጅን ኃይል አማራጭ አቅም ለዓለም ለማሳየት ዳግም ወደ ስፍራው ተመልሷል።
ለዚህ ታሪካዊ ሙከራ የሚነዳው ጄሲቢ ሃይድሮማክስ "JCB Hydromax" የተባለው መኪና 9.75 ሜትር ርዝመት ያለው፣ ደማቅ ቢጫ ቀለም የተቀባ እና ልክ እንደ እርሳስ ረጅምና ቀጭን ቅርጽ ያለው ነው።
መኪናው ከሁለት የሃይድሮጅን ውስጣዊ የማቃጠያ ሞተሮች የሚመነጭ 1 ሺህ 600 የፈረስ ጉልበት ያለው ሲሆን፣ የተጨመቀ የሃይድሮጅን ጋዝን ከአየር ጋር በማቀላቀል እጅግ ግዙፍ አቅም ያመነጫል።
ባለፈው ሳምንት በተደረገ የልምምድ ሙከራ አሽከርካሪው በሰዓት 592.7 ኪሎ ሜትር ፍጥነት መድረስ የቻለ ሲሆን፣ ይህን አስደናቂ ፍጥነት እንደ ይፋዊ ሪከርድ ለማስመዝገብ በዓለም አቀፉ የሞተር ስፖርት አስተዳደር ተቋም ታዛቢዎች ፊት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
የዚህ ሙከራ ዋና ዓላማ የድሮውን የናፍጣ ሪከርድ መስበር ብቻ ሳይሆን፣ እስካሁን በሃይድሮጅን ለሚሰሩ መኪኖች እና ለኤሌክትሪክ መኪኖች ተይዘው የቆዩትን የፍጥነት ሪከርዶች በአንድ ጊዜ ማሻሻል ነው።
ይሁን እንጂ የዘንድሮው ሙከራው በአውሮፓውያኑ 1997 ዓ.ም በኔቫዳ በረሃ መንትያ ጄት ሞተር ባለው መኪና በሰዓት 1,227.9 ኪሎ ሜትር በመብረር የድምፅን ፍጥነት ከሰበረበትና አካባቢውን ካናወጠበት ታሪካዊ ፍጥነት ጋር እንደማይገዳደር እርግጥ ነው።
አሽከርካሪው መንሸራተት በሚበዛበት የጨው ንጣፍ ላይ መኪናውን ለማቆም የፓራሹት አጠቃቀምን ጨምሮ ተሽከርካሪው ላይ ጥብቅ የደህንነት ልምምዶችን ለወራት አድርጓል።
በተለይም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ የፍጥነት ሙከራ ላይ ክሪስ ራሽኬ የተባለ አሽከርካሪ ህይወቱን ማጣቱን ተከትሎ የዘንድሮው የደህንነት ጥንቃቄ እጅግ ጥብቅ ሆኗል።
ከ1914 ዓ.ም ጀምሮ የበርካታ የፍጥነት ሪከርዶች መሞከሪያ የሆነው እና እንደ “Independence Day” ያሉ ታዋቂ ፊልሞች የተቀረጹበት ይህ የቦኔቪል የጨው ሜዳ፣ ተመልካቾች ከ16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ካለው የመሮጫ መስመር 400 ሜትር ርቀው በአጉሊ መነጽር ብቻ እንዲመለከቱ ያስገድዳል።
ከሜዳው ስር ያለው ውሃ የመኪናውን ጎማዎች ለማቀዝቀዝ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን፣ አንዲ ግሪንም የበረሃውን ሙቀት ለማምለጥ ፀሐይ እንደወጣች ታሪካዊ ሙከራውን ይጀምራል።
በቃልኪዳን መዓድን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: