አውስትራሊያ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን ይበልጥ ለማስፋፋት በማሰብ በንግድ እና በግብርና ተቋማት ላይ የሚገጠሙ የጣሪያ ሶላር ፓነሎች ወጪን በ20 በመቶ የሚቀንስ አዲስ የድጎማ ፕሮግራም ይፋ አድርጋለች።
ይህ ወቅታዊ እርምጃ የተቋማቱን የኃይል ወጪ ለመቀነስ እና የካርቦን ልቀትን ለመግታት የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ዋነኛ አካል መሆኑ ተገልጿል።
በአዲሱ ፕሮግራም መሠረት መንግሥት የሚያደርገው የድጎማ ሽፋን የሶላር ስርዓት መጠኑን ከ100 ኪሎዋት ወደ 1 ሜጋዋት ከፍ የሚያደርግ ነው።
ይህም ትልልቅ ፋብሪካዎች፣ መጋዘኖች፣ የእርሻ ማዕከላት እና ሌሎች የንግድ ተቋማት ከዚህ ቀደም አግኝተውት የማያውቁትን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ሰፊ ዕድል ይፈጥርላቸዋል።
የአገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥና ኃይል ሚኒስትር ክሪስ ቦወን እንዳብራሩት፣ የሶላር ፓነሎች ግጠማ ወጪ መቀነሱ የንግድ ተቋማት በየጊዜው የሚከፍሉትን የኤሌክትሪክ ክፍያ በከፍተኛ ሁኔታ ያቀልላቸዋል።
ይህ ደግሞ ተቋማቱ ለሥራ ማስፋፊያ እና ለምርታማነት እቅዶቻቸው የሚውል ተጨማሪ ፋይናንስ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል ብለዋል።
አውስትራሊያ በዓለም ላይ በቤት ውስጥ የሶላር አጠቃቀም ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአማካይ ከሦስት ቤቶች አንዱ የሶላር ፓነል ተጠቃሚ ነው።
አሁን ደግሞ መንግሥት ይህንን አስደናቂ ስኬት ወደ ንግድና ግብርና ዘርፎች በማስፋፋት የንጹህ ኃይል ሽግግሩን ለማፋጠን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ታውቋል።
በቃልኪዳን ማዕድን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: