በተፈጥሮ የሥነ-ክዋክብት ክስተቶች መሀል እንኳን ምን ያህል ተሰጥኦን ለማሳየት መሞከር እንደሚቻል ያሳየ አንድ ልዩ ክስተት በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል።
ይህ ክስተት በስፔናዊው የኦሊምፒክ የስኬትቦርድ ተወዳዳሪ ዳኒ ሌኦን አማካኝነት የተደረገ ሲሆን፣ በተከሰተው ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ወቅት ሰዓቱን በትክክል ጠብቆ ባከናወነው ድንቅ ዝላይ የስፖርቱን እና የሥነ-ከዋክብት ወዳጆችን እጅግ አስገርሟል።
ይህ ድንቅ ትዕይንት የተከናወነው ነሐሴ 6 ቀን 2018 ዓ.ም በስፔን፣ አይስላንድ እና አርክቲክ ውቅያኖስ አካባቢዎች በታየው ታሪካዊ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ወቅት ነው።
ይህ የፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ ፀሐይን ሙሉ በሙሉ በመጋረድ በቀን ድቅድቅ ጨለማ የፈጠረችበትና የፀሐይ አክሊል (ኮሮና) በጉልህ የታየበት ብርቅዬ የተፈጥሮ ክስተት ሲሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀልብ የሳበ ነበር።
በዚህ ድቅድቅ ባለችው አጭር ቅጽበት፣ ዳኒ ሌኦን ከዝላይ መነሻው (ራምፕ) በመንጠራራት፣ ከጨለማው ሰማይ ጋር ተዋህዶ በፀሐይ ፊት ለፊት የሚበር በሚመስል መልኩ አስደናቂ እይታን ማሳየት ችሏል።
በግርዶሹ ወቅት ከጨረቃ እና ከፀሐይ ፊት በማለፍ ጋር በትክክል እንዲገጥም ተደርጎ መሰላቱ ትዕይንቱን ሌላ አስገራሚ ጥበብ አድርጎታል።
በቶኪዮ 2020 እና በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ስፔንን ወክሎ የተወዳደረው ይህ ስኬትቦርደር፣ አስደናቂውን ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ በማጋራት "የሕይወቴ ታላቅ እንቅስቃሴ" ሲል ገልጾታል።
ይህ ዝላይ (ትሪክ) በድንገት የተከናወነ እንዳልሆነና ከፍተኛ ዝግጅት እንደተደረገበት የተጋራው ቪዲዮ እና ምስል በግልፅ ያሳያል።
በስፖርት እና በተፈጥሮ ድንቅ ክስተት ውህደት የተፈጠረው ይህ አስደናቂ ጥበብ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መጋራቱን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ የብዙዎችን ትኩረት በፍጥነት መሳብ ችሏል።
ትዕይንቱ የትኛውም ጊዜና ሁኔታ ተሰጥኦን ከማሳየት እንደማይገድብ ከተፈጥሮ ጋር በማዋሃድ ያሳየ ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኗል።
በሲሳይ መንግስቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: