ዛሬ በመላው ዓለም የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የወጣቶችን ያልተገደበ አቅም፣ የፈጠራ ክህሎት፣ የጽናት መንፈስ እና የሁለንተናዊ ለውጥ አራማጅነት በድምቀት የሚዘከርበት ታላቅ ዕለት ነው።
ይህ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጣቶች የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ሽግግር ዋና መሪዎች መሆናቸውን በማስመር የወደፊቷን ዓለም በዘላቂነት፣ በአረንጓዴ ልማት እና በዲጂታል ዕውቀት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያላቸውን መተኪያ የሌለው ድርሻ ጎልቶ የሚወጣበት አጋጣሚ ነው።
በኢትዮጵያም የወጣቱ የዕድሜ ስብጥር የሕዝቧን ከፍተኛ ቁጥር የሚይዝ በመሆኑ ይህንን ግዙፍ የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት ኃይል ወደ ተጨባጭ ልማት እና ብልፅግና መለወጥ የትውልዱም ሆነ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ቀጥሏል።
ወጣቶች የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች ብቻ ሳይሆኑ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋና የልማት፣ የኢኖቬሽን፣ የሰላም ግንባታ እና የማኅበራዊ ዕድገት መሪዎች ናቸው።
ኢትዮጵያን ከወጣቶቿ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በዚህም ወጣቶች ለብልጽግና፣ ለሉዓላዊነት እና ለሁለንተናዊ ዕድገት ያላቸው ሚና ወሳኝና የማይተካ ነው።
የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት፣ የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት እና የአመራርነት ሚና ለማጠናከር በተለይም የመደመር መንግሥት በልዩ ትኩረት እና በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለወጣቱ ትውልድ ያላቸው አመለካከት በከፍተኛ ተስፋ እና እምነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ "ይህንን ትውልድ በአዲስ ዕይታ ነው የማየው፤ ትልቅ ተስፋ ይሰጡኛል፤ እጅግ የበቁ ናቸው፤ የአስተሰብ እና የመረዳት አቅማቸው ከቀደሙት ትውልዶች በግልጽ የተለየና የላቀ ነው" በማለት ለወጣቶች ያላቸውን ጥልቅ ክብርና ጽኑ እምነት ይገልጻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቱን የነገይቱ ኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊ እና የብልፅግና መሠረት አድርገው በመውሰድ፣ ትውልዱ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታንጾ ለታላቅ ሀገራዊ ዓላማ እንዲቆም ሁለንተናዊ ዝግጅቶችን በመምራት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በይፋ የጀመረችው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ዝርጋታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በጥልቀት እየቀየሩት ይገኛሉ።
የዲጂታል መታወቂያ ፋይዳ፣ የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች፣ የኢ-ኮመርስ እና የዲጂታል የመንግሥት አገልግሎቶች መስፋፋት ለወጣቱ ሰፊ የሥራ እና የፈጠራ ዕድል ፈጥረዋል።
በዚህ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ዋና የለውጥ አራማጅ እና ተጋሪ የሆነው ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል አዳዲስ ፈጠራዎችን በማቅረብ፣ የቴክኖሎጂ ስታርታፖችን በመመሥረት እና አሠራሮችን በማዘመን የዲጂታል ኢኮኖሚውን በግንባር ቀደምትነት እየመራው ይገኛል።
ለዚህ ታላቅ የዲጂታል ጉዞ በዋና ማፋጠኛነት የተዘጋጀው "የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ" የኢትዮጵያን ወጣቶች በዲጂታሉ ዓለም ተወዳዳሪ እና አቅም ያላቸው ለማድረግ የተቀረፀ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኮድ ማድረግ የኮድ መስመሮችን መጻፍ ብቻ ሳይሆን ችግር ፈቺነት፣ ሂሳዊ አስተሳሰብ እና የፈጠራ አቅም ግንባታ ነው" በማለት ባስገነዘቡት መሠረት፣ ወጣቶች የክረምቱ ወቅት ከመጠናቀቁ በፊት ይህንን የኮደሮች ኢኒሼቲቭ በመቀላቀል የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ 7 ሚሊዮን እንዲያደርሱ ሀገራዊ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ኢኒሼቲቭ በኮዲንግ፣ በዳታ ሳይንስ፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና በዌብ ልማት ዘርፎች ሚሊዮኖችን በማሠልጠን፣ ወጣቶች ከሀገር ውስጥ አልፈው በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ላይ በብቃት እንዲሰማሩ እና የዲጂታል ብልፅግናን እውን እንዲያደርጉ ሰፊ መንገድ ከፍቷል።
በመሆኑም የወጣቶች ቀን ዝግጅት ከመከበር አልፎ፣ እያንዳንዱ ወጣት ያልተነካ አቅሙን የሚያወጣበት፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ክህሎቶችን የሚያከማችበት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዕድገት የማይጠፋ አሻራውን የሚያስቀምጥበት ጥሪ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች በዲጂታል ዕውቀት እና በሥራ ወዳድነት ታንጸው፣ ከከፋፋይ እና ከአሉታዊ ንትርኮች በመራቅ የነገዋን የበለፀገች እና የታፈረች ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደርጉት ጉዞ ጥረታቸው እና የሚከፍሉት መስዋዕትነት ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ ነው።
በትውልዱ ትከሻ ላይ የተጣለው ሀገራዊ አደራ ታላቅ ቢሆንም በዕውቀት፣ በጽናት እና በመደመር እይታ የታጠቀው የዛሬው ወጣት ይህንን አደራ በብቃት ተወጥቶ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን እንደሚያደርግ ሙሉ እምነት ተጥሎበታል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: