የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባቀደውና በተጠበቀው ልክ ሂደቱን በስኬት እያካሄደ እንደሚገኝና አጠቃላይ የሥራውን ሦስት አራተኛ ማጠናቀቁን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ አብራርተዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የሂደቱን ደረጃ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እያንዳንዳቸው 500 ተመካካሪዎችን ያቀፉ ስምንት የምክክር ቡድኖች ጥልቅ ውይይት ሲያካሂዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል። አብዛኞቹ ቡድኖችም በተነሱ የምክረ ሀሳቦች ላይ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ እና ፊርማቸውን በማኖር ሥራቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ።
በውይይት ሂደቱ ውስጥ አለመግባባቶችና የሃሳብ ግጭቶች ቢያጋጥሙም፣ እነዚህ ሁኔታዎች መከሰታቸው የምክክሩን አስፈላጊነት ይበልጥ ያረጋገጠ መሆኑን ኮሚሽነሯ አስገንዝበዋል። ተመካካሪዎቹ ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ የውይይት መንገድ በመፍታትና እርስ በእርስ በመደማመጥ ወደ አንድ አማካይ የጋራ ሀሳብ መምጣት መቻላቸው ትልቅ ስኬት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ስምንቱ የምክክር ቡድኖች ያዘጋጇቸውንና የተስማሙባቸውን የምክረ ሀሳቦች የማጣጣም ሥራ የሚሰራ ልዩ ቡድን መቋቋሙ ተገልጿል።
ይህ ቡድን በሚቀርቡት ሃሳቦች መካከል የሚጣረሱ ነጥቦች እንዳይኖሩ ጥንቃቄ ከማድረግ ባለፈ፣ ልዩነት የታየባቸውን ሀሳቦች ወደ አንድ በማምጣት እና አጠቃላይ ሀሳቦቹ ላይ ወጥነት የመፍጠር ወሳኝ ሥራ ያከናውናል።
በሌላ በኩል ከሂደቱ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ኮሚሽኑ በተዘረጋው የቅሬታ መፍቻ ሥርዓት መሠረት እየተቀበለና እያጠና ውሳኔ እንደሚሰጥበት አረጋግጧል።
ለረጅም ጊዜ ሲደከምበት የቆየው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ውጤታማነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚበሰርበት ቀጣዩ ታሪካዊ ምዕራፍ በቅርቡ እንደሚጀምር ኮሚሽነሯ ጥቆማ ሰጥተዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: