ኢትዮጵያን በቱሪዝም ስናስብ በአዕምሯችን የሚመጡት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የጎንደር ቤተ መንግሥቶች፣ የሰሜን ተራሮች እና የረጅም ዘመን ታሪክ የሚያስታውሱ ቅርሶች ናቸው።
እነዚህ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያዎች ሆነው ለዓለም ሀገራችንን ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል። ዛሬ ግን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ካርታ ከታሪካዊ ቅርሶቿ ባሻገር እየሰፋ መጥቷል። ተፈጥሮን፣ ባህልን፣ መዝናኛንና ዘመናዊ የቱሪዝም ልማትን ያቀናጁ አዳዲስ መዳረሻዎች በመፈጠር ላይ ናቸው። ይህም ኢትዮጵያ በጥቂት የቱሪዝም መዳረሻዎች ብቻ የምትታወቅ ሳትሆን፣ በብዙ አስደማሚ ስፍራዎች የተሞላች የቱሪዝም ሀብት እንዳላት የሚያሳይ ነው።
ላሊበላ፣ አክሱምና ጎንደር የሀገራችን ረጅም ታሪክ፣ ሥልጣኔና ባህላዊ ቅርስ የሚያስመሰክሩ የቱሪዝም መለያዎች ሆነው ሲቀጥሉ፡- ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ እንጦጦ፣ አንድነት ፓርክና ሶርጋ ኢኮ-ሎጅ ያሉ መዳረሻዎች ደግሞ የኢትዮጵያን የቱሪዝም አማራጭ በአዲስ መልክ እያስፋፉ ይገኛሉ።
እነዚህ ስፍራዎች የተፈጥሮ ውበትን፣ የአካባቢ ባህልን፣ የመዝናኛ እድሎችን እና ዘመናዊ መሠረተ ልማትን በማቀናጀት ቱሪስቶች ኢትዮጵያን በአንድ ጉዞ መዳረሻ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ልምዶች እንዲያውቋት ዕድል ይፈጥራሉ።
በተለይ ጎርጎራ የሐይቅ ዳርቻን ውበት፣ የተፈጥሮ ሃብትን በማጣመር የባሕር ዳርቻ ቱሪዝምን በአዲስ እይታ ለማቅረብ የሚያስችል መዳረሻ በመሆን፣ ወንጪ ደግሞ የእሳተ ገሞራ መልክዓ ምድር፣ የሐይቅ ውበት እና የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ሀብት የሚያጣምር ልዩ የቱሪዝም ስፍራ ሆኖ ተገንብቷል።
በአዲስ አበባ ያሉት እንጦጦና አንድነት ፓርክ ደግሞ፣ የከተማ ቱሪዝምን ከተፈጥሮ፣ ከታሪክ፣ ከመዝናኛና ከባህላዊ ልምድ ጋር የሚያጣምሩ የከተማ ውስጥ መዳረሻዎች ሆነዋል።
ቀደም ሲል በቂ ትኩረት ያላገኙ የተፈጥሮ ሀብት የሆኑትን የሐይቅ ዳርቻዎች፣ ተራራማ መልክዓ ምድሮች፣ የደን ሀብቶች እና የአካባቢ ባህላዊ ሀብቶች በተገቢው መሠረተ ልማትና አገልግሎት ሲደገፉ የጎብኝዎች መስህብ ወደሆኑ የቱሪዝም ማዕከላት ተቀይረዋል።
በዚሁም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ታሪክ አሁን ላይ በአዲስ ምዕራፍ ላይ ሲሆን፣ የቆዩት የቱሪዝም መስህቦች የሀገራችንን ታሪክና ሥልጣኔ ለዓለም ሲነግሩ፣ አዳዲሶቹ መዳረሻዎች ደግሞ የኢትዮጵያን ተፈጥሮ፣ ዘመናዊነትና የልማት አቅም እያሳዩ ናቸው።
ይህ የቱሪዝም መዳረሻዎች መበራከት ጎብኝዎች አንድን ቦታ ብቻ አይተው ከመመለስ ይልቅ በበርካታ ክልሎችና ከተሞች የተለያዩ ልምዶችን እንዲያገኙ ዕድል በመፍጠር ታሪክና ተፈጥሮ፣ ባህልና መዝናኛ፣ ተራራና ሐይቅ፣ በአንድ የጉዞ ካርታ ላይ ሲገናኙ ኢትዮጵያ የምትሰጠው የቱሪዝም ልምድ ይበልጥ ሰፊና የተለያየ ይሆናል።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ትልቁ ትርጉም አዳዲስ ስፍራዎችን መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ የነበሩትን ሀብቶች በአዲስ ዓይን ማየትና ለትውልድ እንዲጠቅሙ በዘላቂነት ማልማት ነው። ከላሊበላ እስከ ጎርጎራ፣ ከአክሱም እስከ ወንጪ፣ ከጎንደር እስከ ኮይሻ፣ ከእንጦጦ እስከ አንድነት ፓርክ እና ከተፈጥሮ መዳረሻዎች እስከ ኢኮ-ቱሪዝም ስፍራዎች ድረስ የሚዘረጋው ይህ ሰፊ የቱሪዝም ካርታ ኢትዮጵያ የምትኮራበት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬ እየፈጠረች ያለችውን አዲስ የቱሪዝም ትርክትም ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከአንድ መዳረሻ ወደ ሺህ አስደማሚ ስፍራዎች የምትጓዝበት ጉዞ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ታሪክ የትናንትን ቅርስ ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬን ፈጠራና የነገን ተስፋ የሚያቀናጅ ትልቅ የልማት ታሪክ እየሆነ መጥቷል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: