የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ በሽታ ሆኖ የቆየው አንዱ "የዘመን እስረኝነት" ነው። የፖለቲካ ልሒቁ ዛሬ ላይ ቆሞ ወደፊት ከመራመድ፣ ነገን ከማለም ይልቅ፣ በትናንትናው መነጽር ዛሬን ሲዳኝ፣ ከትናንት ትዝታ ጋር ተጠባቆ ወይ በብሶት ወይ በትዝታ ምኞት የትናንት የፖለቲካ ትርክትን ሲያመነዥክ ኖሯል። በሞተ ትናንት ውስጥ ህይወት ለመዝራት ሲሯሯጥ ዛሬም ያልፈውና፣ ከሞተውም ትናንት፣ ካለውም ዛሬ ተጣልቶ ትውልድም ግራ ይታያል።
ያለፈን ቁስል ዛሬ ማከክና ለዛሬ ፍርድና ጥፋት ማላከኪያ (scapegoat) ማድረግ የዘመን ታካካነት ጉልህ መለያ ነው። ትናንት የራሳቸውን ጊዜ በአሉታም ሆነ በአዎንታ ተጠቅመው ባለፉ ትውልዶች ጉዳይ የሚበዛውን ጊዜ በማጥፋት ዛሬ በእጁ ያለውን ወርቅ እድል አሳልፎ ይሰጣል። ትናንት ለዛሬ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እስከሌለው ድረስ ከመማርያነት ባለፈ ዛሬ ላይ ተፅዕኖ እንዲኖረው የሚፈቅድ ትውልድ የራሱን እንቁ እድል አሳልፎ የሰጠ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደ ቤተ-ሙከራ በርካታ የውጭ ርዕዮተ-ዓለማትን ስትፈትሽና ስትሞክር የኖረች ሀገር ብትሆንም፣ እነዚህ ከውጭ የተቀዱ ጽንሰ-ሐሳቦች የሀገራችንን ብዝኃነት፣ ባህልና የሕዝብ ሥነ-ልቦና ያላገናዘቡ በመሆናቸው ኢትዮጵያን ወደ ጥልቅ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራት መርተዋታል። በዚህ ውስብስብ የታሪክ መስቀለኛ መንገድ ላይ፣ የዘመናት የፖለቲካ እክሎችን ፈትቶ ሀገርን ወደፊት የሚያራምድ "መደመር" የተሰኘ ሀገር በቀልና ስር-ነቀል የዕይታ ማዕቀፍ እንደ ብርሃን ፈንጥቋል።
መደመር ኢትዮጵያ ስትሽከረከርበት ከነበረው የዜሮ ድምር ፖለቲካ እና የመጠፋፋት አዙሪት በማውጣት፣ ውጫዊና ውስጣዊ አቅሞቿን አሰባስባ ወደፊት እንድትገሰግስ የሚያደርግ ተፈጥሯዊ የለውጥ ጉልበት ነው። መደመር የዘመን እስረኝነት የተጣባውን የፖለቲካ ባህል ሰብሮ ወጥቷል።
የመደመር ትውልድ ካለፈው ስህተት ይማራል እንጂ በትናንት እስር ቤት አይታሰርም። የትናንት ወረቶችን እንደ ሀገር ግንባታ ዋልታና ማገር በመጠቀም ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሰረት ይጥላል። ይህ ጥልቅ ፍልስፍና የሀገራችንን ስብራት የሚጠግነው ትናንትን በማፍረስ ሳይሆን፣ ካለፉት ዘመናት የወረስነውን "ወረት" ይኸውም ታሪካዊ ልምድ፣ የዳበረ ተሞክሮ፣ ሥነ-መንግሥታዊና ባህላዊ እሴቶችን አቧራ አራግፎ ለዛሬው የሀገር ግንባታ መሰረት በማድረግ ነው።
የትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል ሳያገል፣ ሁሉም ማኅበረሰብ ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ ነው በሚል የድምር እሳቤ፣ የከረሩ የፖለቲካ ግፊቶችን በማለዘብ ለእርስ በእርስ ግጭት ይባክን የነበረውን ጉልበት ወደሚያግባባ የስበት ማዕከል ያመጣዋል።
በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረውን ሐሳብ አዋህደን ስንመለከተው፣ መደመር እንደ ጠባብ ርዕዮተ-ዓለም በአንድ ቦታ ላይ የሚቸነከር ቀኖና ሳይሆን፣ በጊዜውና በሁኔታው ራሱን እያደሰ አዳዲስ የመፍትሄ ሐሳቦችን ያለማቋረጥ የሚያፈልቅ "ገቢር ነበብ" (ፕራግማቲክ) የሆነ ተራማጅ እይታ ነው። ይህ ፍልስፍና የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ክብርና ብልጽግና ማዕከል ያደረገ ሲሆን፣ ከሌሎች ከውጭ ከመጡ ርዕዮተ-ዓለማት የሚለየው በተግባራዊነቱ እና ሁሉንም አሰባሳቢ በሆነው ሚዛናዊነቱ ነው።
የተፈጥሮ ህግ የሆነውን ተቃርኖ ለማጥፋት ከሚሞክሩ አክራሪ ፍልስፍናዎች በተቃራኒ፣ ተቃርኖዎችን ወደ ተደማሪ የለውጥ ጉልበትና ወደ "ወርቃማ አማካይ" መንገድ ይቀይራል። በኢትዮጵያ የነበረውን የሲቪክ ብሔርተኝነትን (በግለሰብ መብት ላይ የሚያተኩር) እና የማኅበረሰብ ብሔርተኝነትን (በቡድን መብት ላይ የሚያጠነጥን) ጽንፎችን በማስታረቅ፣ ሁለቱንም በእኩል ሚዛን የሚያስተናግድ "የመግባባት ዴሞክራሲን" እውን ለማድረግ ይተጋል።
ይህ አካሄድ ልዩነትን እንደ ስጋትና አደጋ ሳይሆን፣ እንደ ውበትና የጥንካሬ ምንጭ አድርጎ የሚቀበል፣ ተቃርኖንም አላግባብ ከሚባክን ግጭት ወደ አንድ "የኃይል ብዜት" (Synergy) የሚቀይር የጥበብ መንገድ ነው።
በዓለማችን ፈጣን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ለውጥ ያስመዘገቡት እንደ ምስራቅ እስያ ያሉ ሀገራት፣ የውጭን ሞዴል እንዳለ ከመገልበጥ ይልቅ የራሳቸውን ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶች ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማዋሃድ ነው ለውጥ ያመጡት። መደመርም በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ የውጭን ቀኖና አይጭንም። ይልቁንም የኢትዮጵያን ነባር ባህላዊ የዴሞክራሲ እርሾዎች፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶች አቧራ በማራገፍ፣ ከዓለም አቀፍ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ልምዶች ጋር ደምሮ ለሀገራችን ችግሮች ፍቱን መፍትሄ ያበጃል።
ተቋማዊ ስብራትን በመጠገን የዴሞክራሲና የሀገረ መንግሥት ቀጣይነት ዋስትና የሆኑ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት የመደመር አንዱ ምሰሶ ነው። መደመር ለኢትዮጵያ የኅልውና ዋስትና፣ የስብራት መጠገኛ፣ ነው። ጠብመንጃን እና ጉልበትን እንደ ብቸኛ የመፍትሄ መንገድ ከሚያየው ኋላቀር የፖለቲካ ባህል እንዲሁም ከ"መንጋነት" (Herd mentality) አስተሳሰብ ተላቅቆ፤ በሐሳብ ልዕልና እና በይቅርታ ላይ የተመሰረተ የሲቪክ ባህልን ይገነባል።
በተለይም በድህረ-እውነት ዘመን (Post-truth era) የመረጃ ማዕበል እውነታን በሚያዛባበትና ፅንፈኝነት በሚስፋፋበት ወቅት፣ መደመር ሚዛናዊ የአደባባይ ምሁራንን ሚና ከፍ በማድረግ፣ ማኅበረሰቡን ከስሜታዊነት ይልቅ ወደ ምክንያታዊነት ይመራል። ይህ ጥልቅ ፍልስፍና የኢትዮጵያን ብዝኃነት በብቃት እያስተዳደረ፣ ሀገራችንን ከዘመን እስረኝነት አላቆ ወደማይቆም የልማትና የስልጣኔ አብዮት የሚያሸጋግር ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ፀጋ ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: