Search

ቀይ ባሕር ከታሪካዊ የይገባኛል ጥያቄ ባሻገር ለቀጣናዊ ሰላምና የጋራ እድገት

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 77

በዓለም አቀፉ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ12 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው የዕቃ ዝውውር በሚያልፍበትና የዓለም ኃያላን አገራት የጦር ሠፈራቸውን ባደራጁበት በቀይ ባሕር ቀጠና፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጎላ የጂኦፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኗል።

ይህ ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን ከታሪክ ማኅደር የሚቀዳ ሕጋዊ መብት፣ በዓለም ትልቋ ባህር በር የሌላት እና የ130 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ ለሆነችው አገር የሕልውና ዋስትና እንዲሁም ለአጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ዕድገት የሚበጅ የሰላም ጥሪ ነው።

ታሪክ እንደሚመሰክረው ጥንታዊው የአክሱም ኢምፓየር በዓለም ላይ ከነበሩ አራት ኃያላን መንግሥታት አንዱ ሆኖ እንዲገነባ ቁልፍ ሚና የተጫወተው በቀይ ባሕር ላይ የነበረው የአዱሊስ ወደብ ነው።

ይህች ወደብ የቅንጦት ዕቃዎች የሚተላለፍባትና ከሮም፣ ፋርስና ሕንድ የመጡ መርከቦች የሚያርፉባት ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ነበረች። አስተዳደሩ በመካከለኛው ዘመንም "ምድር ባሕሪ" በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ ነገሥታት ግብር እየተቀበሉ የመሩት ቀጠና ነበር።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓውያን የ"አፍሪካ ቅርጫ" ሽሚያና የግብፅ ወረራ ሲጀመርም አፄ ዮሐንስ አራተኛና ራስ አሉላ አባ ነጋ የግብፅን ጦር በጉንደትና በጉራዕ ድል በማድረግ የባሕር ዳርቻውን ሉዓላዊነት አስከብረዋል።

በ1884ቱ የአድዋ ውልና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም የተመድ ውሳኔ 390 (4) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ያለውን ፍላጎት በግልጽ ያመነባቸው ታሪካዊ እውነታዎች ናቸው።

ከታሪካዊ ፍትሕ ባሻገር የኢትዮጵያ ጥያቄ በዘመናዊ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ላይ በጥብቅ የተመሠረተ ነው። አገራችን የተመድ የባሕር ሕግ ስምምነት ፈራሚ ስትሆን የስምምነቱ አንቀጽ 125 ወደብ አልባ አገሮች ወደ ባሕር የመውጣትና በትራንዚት አገሮች ግዛት ውስጥ በማንኛውም የትራንስፖርት አማራጭ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

አንቀጽ 127 ደግሞ በወደብ አልባ አገራት ንግድ ላይ ያላግባብ የጉምሩክ ቀረጥ እንዳይጣል ይከለክላል። ስለዚህ አገራችን የምታነሳው ጥያቄ የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ሳይሆን ዓለም አቀፉ ሕግ የሰጣትን መብት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የመጠቀም ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ ምክንያት የምትከፍለው የውጭ ምንዛሪና የስትራቴጂካዊ ተጋላጭነት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነው። ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ከ95 በመቶ በላይ የባሕር ንግዷን በአንድ ወደብ ላይ ጥገኛ ማድረጓ ብሔራዊ ደኅንነቷን ሥጋት ላይ ጥሎታል።

ለጅቡቲ ወደብ በዓመት የሚከፈለው ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪራይ የአገራችንን ልማት ክፉኛ እየጎዳ ሲሆን ይህ በየሦስት ዓመቱ አንድ 'ታላቁ የሕዳሴ ግድብ'ን ሊያስገነባ የሚችል ግዙፍ ሀብት እንደማጣት የሚቆጠር ነው።

የባሕር በር ማግኘት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው። በኢኮኖሚው ዘርፍ 'የወደብ አልባነት ታክስን' በማስቀረት ለአርሶ አደሩ የሚመጣውን ማዳበሪያና መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በመቀነስ የኑሮ ውድነትን ያቀልላል።

በወጪ ንግዱም አገራዊ ምርቶች በዝቅተኛ የትራንስፖርት ወጪ ለዓለም ገበያ ቀርበው ተወዳዳሪነታቸውን ያረጋግጣሉ። ይህ የኢኮኖሚ ጥንካሬ ከስትራቴጂካዊ ደኅንነት ጋር ሲቀናጅ የንግድ መርከቦችን ከባሕር ላይ ወንበዴዎች ሥጋት በራስ አቅም ለመጠበቅና ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና ያላትን የዲፕሎማሲ ሚና ከፍ ለማድረግ ያስችላል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሰላም፣ በዲፕሎማሲና በጋራ ልማት ላይ የተመሠረተ ነው። የኢትዮጵያ ወደ ባሕር መመለስ ጎረቤቶቿን የሚጎዳ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ የጋራ ንግድ እንዲያብብና ቀጠናው ራሱን የቻለ ጠንካራ የኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል ትልቅ አቅም ነው።

ወደፊትም ቢሆን ይህንን ታሪካዊና ሕጋዊ መብት በሰላማዊ ድርድርና በቀጣናዊ ትብብር መርህ በማስቀጠል፣ የኢትዮጵያን ትክክለኛ የባሕር ባለድርሻነት ማረጋገጥ የነገው ብሩህ ተስፋችን ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: