Search

የጉምሩክ ምክትል ኮሚሽነሩን ጨምሮ በከባድ የሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 53 ግለሰቦች ላይ ፍርድ ቤት የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 72

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ 14 ባለሙያዎች እና ግብረ አበሮቻቸው፣ እንዲሁም 39 የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ተባባሪ ነጋዴዎች ናቸው።

እነዚህ ግለሰቦች ከጉምሩክ እና ከገቢ አሰባሰብ አሰራር ጋር በተያያዘ የአሰራር ስርዓትን በመጣስ፣ የታክስ ምዘናዎችን ባልተገባ ሁኔታ በመቀነስ፣ የሐሰት ደረሰኞችን በማጽደቅ፣ የኮምፒውተር ሥርዓት መረጃዎችን በመሰረዝና በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረዋል።

በችሎቱ ላይ መርማሪ ፖሊስ የተፈጸመው ወንጀል የኮሚሽኑና የቢሮው ኃላፊዎች ከሌሎች ባለሀብቶችና ነጋዴዎች ጋር በመደራጀት ያካሄዱት ሰፊ እና ውስብስብ የኢኮኖሚ አሻጥር መሆኑን አስረድቷል።

በመሆኑም የበርካታ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ እስካሁን ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸውን በቁጥጥር ስር ለማዋል፣ ከተለያዩ ተቋማት ተያያዥ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ እና በመንግሥት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በኦዲት ለማረጋገጥ በ53ቱም ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ድርጊቱ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተደረሰበት መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮችን ሊያባብሉ እና ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው ሰነዶችን ሊያጠፉ ይችላሉ በሚል የዋስትና ጥያቄውን አጥብቆ ተቃውሟል።

በሌላ በኩል የተጠርጣሪ ጠበቆች ፖሊስ ያቀረበው ጥርጣሬ በጥቅሉ የቀረበና የእያንዳንዱን ተሳትፎ የማይገልጽ መሆኑን እንዲሁም የደረሰው የጉዳት መጠን አለመገለፁን በክርክራቸው ወቅት አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ የተጠርጣሪዎችን የጤና ሁኔታና የማቆያ ቦታ ጥበትን ምክንያት በማድረግ ደንበኞቻቸው በዋስትና ወጥተው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ጠይቀዋል። ሆኖም የግራ ቀኙን ክርክር በዝርዝር ያዳመጠውና የፖሊስን የምርመራ መዝገብ የተመለከተው ችሎቱ፣ በቂ ጥርጣሬ መኖሩን ከመዝገቡ በመረዳት ፖሊስ የጀመረውን ማጣሪያ አጠናክሮ እንዲቀጥል የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

ተጠርጣሪዎቹ በሚዲያዎች ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸው ተጥሶ እንደ ወንጀለኛ ተደርገው እየቀረቡ መሆኑን በቃል ላቀረቡት አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ክሳቸውን በፅሁፍ እና በማስረጃ እንዲያቀርቡ አዟል። ችሎቱም መዝገቡን ለመመልከት ለነሐሴ 14 እና 15 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በብርቱካን አስናቀ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: