ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ሲያብራሩ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ለውጦች መካከል ንቁ፣ ተለዋዋጭ እና አጀንዳ ፈጣሪ የሆነ ዲፕሎማሲን እየተከተለች መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም የመጀመሪያው መርህ “Active” ወይም ንቁ ዲፕሎማሲ ነው። ዓለም በፍጥነት በምትለወጥበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከለውጦቹ ራሷን አግልላ የምትቆይ ሳይሆን፣ በክስተቶች ላይ በንቃት የምትሳተፍ እና ጥቅሟን በግልጽ የምታስከብር እንድትሆን የሚያስችላትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትከተላለች።
ሁለተኛው ወሳኝ መርህ “Alternative” ወይም የአማራጭ የወዳጅነት አውታር መገንባት የሚለው ነው። ኢትዮጵያ በጥቂት ሀገራት ላይ ብቻ የተመሰረተ ግንኙነት ከመከተል ይልቅ፣ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ዘላቂ እና ተጨባጭ የጋራ ጥቅም ያላቸውን ሰፋፊ ግንኙነቶች ማስፋት እንዳለባት ሐሳቡ ያመለክታል። የዚህ ዋነኛ ዓላማም በችግር፣ በውጥረት እና በደስታ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙ ታማኝ ወዳጆችን በስፋት ማፍራትና ማቆየት ነው።
ሦስተኛው መርህ “Adaptive” ወይም ተለዋዋጭና ለሁኔታዎች የሚስማማ ዲፕሎማሲ መከተልን ያካትታል። የዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና የኃይል ሚዛን በቀጣይነት እየተለወጠ ባለበት ሁኔታ አንድን አቋም በጥብቅ ብቻ ይዞ መቆም የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ከተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ ጋር እየተጣጣመ እና ከተወሰኑ ቅድመ እሳቤዎች ነፃ ሆኖ የሀገራችንን ጥቅም ማስቀደም እንዳለበት አብራርተዋል።
አራተኛው እና የመጨረሻው መርህ ደግሞ “Agenda” ወይም አጀንዳ ቀራጭ ዲፕሎማሲ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውይይቶች የሌሎችን አጀንዳ ብቻ የምትቀበልና የምታስፈጽም ሳይሆን፣ ለራሷ እና ለመላው አፍሪካ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በንቃት ማምጣት እንዳለባት አስገነዝበዋል።
በዚህም መሠረት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተቋማትና መድረኮች ላይ ፍላጎቷን በግልጽ፣ በቆራጥ እና በድፍረት ማስቀመጥ ያለባት ሲሆን፣ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ፈጣሪነት መሸጋገር የውጭ ግንኙነቷ አንዱ እና ዋነኛው ቁልፍ አቅጣጫ መሆን እንዳለበት በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: