Search

ከስጋት ወደ አጀንዳ መሪነት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ያደረገው አዲሱ የዲፕሎማሲ ጉዞ

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 71

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ "መደመር" በተሰኘው ሀገራዊ እሳቤ አማካኝነት ዓለምን የምታይበትን አዲስ መነጽር ተላብሷል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተተገበረው ይኸው የዲፕሎማሲ ማዕቀፍ፣ የሀገርን ኅልውና እና ክብር ለማስጠበቅ ከቀደሙት ዓመታት የተለየና ስር ነቀል ሽግግር ያደረገበት ነው።

ቀደምት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች በከፍተኛ ሁኔታ "ጎረቤቶቻችን ሊወርሩን ይችላሉ" ወይም "ጠላት ከበበን" በሚል የስጋትና የፍርሃት ትርክት ላይ የተመሠረቱ የነበሩ ሲሆን፣ የአሁኑ የመደመር እሳቤ ግን ይህንን ቀይሮ በራስ መተማመን ላይ የተመሠረተ፣ ብሔራዊ ጥቅምን እና የሀገርን ክብር ማዕከል ያደረገ ገቢር ነቢቢ አካሄድ ሆኗል።

በዚህም አዲሱ የዲፕሎማሲ ጉዞ የሀገራችንን ክብር ከታሪክ ድሎች ባለፈ በዴሞክራሲያዊ ሕጋዊነት እና በኢኮኖሚ ልማት ስኬቶች እየለካ ይገኛል።

በዲፕሎማሲው መስክ አንዱ ሲያተርፍ ሌላው የግድ መክሰር የለበትም በሚለው የጋራ ተጠቃሚነት ወይም “እኔም ልጠቀም አንተም ተጠቀም” መርህ ኢትዮጵያ ጉልህ ስኬቶችን እያስመዘገበች ነው።

በተለይም በዓባይ ወንዝ እና በባሕር በር ጉዳዮች ላይ የሌሎችን ጥቅም ሳትነካ እና የራሷን መብት አሳልፋ ሳትሰጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በፅናት እየሰራች ነው።

የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማንም የውጭ ብድር ሳይሆን በሀገር ውስጥ ፋይናንስ መገንባቱ የሀገራችንን ዲፕሎማሲ በራስ መተማመንና የመደራደር አቅምን ከፍ አድርጎታል።

የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ሳትነካ የራሷን የኤሌክትሪክ ፍላጎት የማሟላት መብቷንም ለዓለም በተግባር አሳይታለች። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት እና በፖለቲካ የመቀራረብና መተባባር ሥራን ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ሲሆን፣ ለኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቀጣናዊ ትሥሥር ፕሮጀክቶች ለዘላቂ ሰላም እና ትብብር ጠንካራ መሠረት እየጣሉ ይገኛሉ።

ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አኳያም ትልቅ የዕይታ ለውጥ ተከስቷል። ለዓመታት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ፖለቲካ ተቃዋሚ ወይም እንደ የገንዘብ ምንጭ ብቻ ይታዩ የነበረውን አሮጌ አመለካከት በመቀየር፣ መደመር ዳያስፖራውን የሀገር አምባሳደር እና የዕውቀት ምንጭ በመዉሰድ የሀገረ መንግስት ግንባታው አካል አድርጎታል።

በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችንም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ወደ ሀገራቸው መመለስ እና መብታቸውን ማስከበር የዲፕሎማሲው ቁልፍ ተግባር ተደርጎ በስፋት እየተተገበረ ነዉ።

በተጨማሪም ዓለም በኃያላን መንግሥታት ሽኩቻ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የአንደኛው ወገን ተከታይ ከመሆን ይልቅ ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል ባደረገ ሚዛናዊ ግንኙነት ከሁሉም ጋር በትብብር መሥራትን መርጣለች።

የኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆን የዚህ ስትራቴጂካዊ አካሄድ ትልቁ ስኬት ነው። ይህ አባልነት ያለፖለቲካዊ ቅድመ-ሁኔታ የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብሮችን ከማስገኘቱም ባለፈ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እና የደቡባዊው ዓለም ድምፅ ሆና እንድትወጣ ትልቅ የጂኦፖለቲካ ተሰሚነት አጎናፅፏታል።

ይህ እሳቤ ሀገራችንን ከጥገኝነት አላቆ፣ የገጠሟትን ስብራቶች በመጠገን፣ በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመች እና ለትውልድ የምትታመን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ሰፊ አቅም ፈጥሮላታል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: