Search

“ኋላቀሩና ወንጀለኛው የህወሓት ቡድን ከግል ጥቅሙ ውጪ ሌላ ዓላማ እንደሌለው በተግባር እያሳየ ነው”፦ ስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 81

ስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ እና በክልሉ ውስጥ እየታዩ ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፣ ኋላቀርና ወንጀለኛ ሲል የጠራው የህወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን ህጋዊ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በመፈንቅለ መንግስት በማፍረስ ቡድኑ የውስጥ ኃይሎችን እንደ ዋና ተላላኪ በመጠቀም ትግራይን "የሲኦል ምድር" አድርጓታል ሲል ኮንኗል።

ይህ ቡድን ከመጀመሪያውኑ የፕሪቶሪያው የሰላም ውል እንዳይተገበርና ሰላም እንዳይጠናከር እሾህ ሲዘራ መቆየቱን ያብራራው ፓርቲው፣ ከግል ጥቅሙ ውጪ ሌላ ዓላማ እንደሌለው በተግባር እያረጋገጠ መምጣቱን አስታውቋል።

የህወሓትን ቡድን የሚያስጨንቀው የህዝብ ደህንነት ሳይሆን የራሱን ጥቅም ማሟላትና የፈጸማቸው ወንጀሎችን ተከትሎ የሚመጣውን ተጠያቂነት ማምለጥ መሆኑንም ጠቁሟል።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያው አሁን እያደረገ ያለው የጦርነት ትንኮሳ መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ የዚህ ቡድን ተፈጥሯዊ ባህሪ ከጦርነት ውጭ መኖር የማይችልና ከሰላም ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑን አስረድቷል። አክሎም ቡድኑ በገጠመው ከባድ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት እንዲሁም ከዓለም ማህበረሰብ በመገለሉ ተስፋ ቆርጦ፣ በግልጽ ሕገወጥ የሽፍትነት ስራ እየፈጸመ ይገኛል ብሏል።

ስምረት ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች የትግራይ የለውጥ ኃይሎች፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች ጋር በመሆን "የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት" ማቋቋማቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ምክር ቤቱ በትግራይ መሽጎ የሚገኘውን ይህንን ኋላቀር ቡድን ለማስወገድ የተጠናከረ ትግል እያደረገ መሆኑን ገልጿል። በመሆኑም ሁሉም ለውጥ ፈላጊ ፓርቲዎች የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ትግላቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርቧል።

በመጨረሻም ይህ ኋላቀር ቡድን "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" በሚል እሳቤ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና ግድያ አጠናክሮ መቀጠሉን ያብራራው ፓርቲው፣ ህዝቡ እያንዳንዱን መረጃ በመያዝ፣ ከለውጥ ኃይሎች ጋር ተደራጅቶ በመታገል የዚህን ጨካኝ ቡድን እድሜ ለማሳጠር የተጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።

የፌዴራል መንግስትና የዓለም ማህበረሰብም የዚህን ፀረ-ሰላምና የቀጣናው ያለመረጋጋት ምክንያት የሆነ ቡድን ለማስወገድ እና ለሕግ ለማቅረብ ለሚደረገው ትግል ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ፓርቲው መልእክቱን አስተላልፏል።

በጎሳዬ /ኪዳን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: