ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔዎች ማህደር እና ያልተነኩ የተፈጥሮ ድንቆች ምድር መሆኗ ይታወቃል። ነገር ግን የዛሬው የቱሪዝም ፍላጎት የታሪክ ቅርሶችን ከሩቅ ከመመልከት አልፎ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ምቹ የመዝናኛ መዳረሻዎችን ይሻል።
በሀገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑት ግዙፍ የመሰረተ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ የቱሪዝም ዘርፉን ከነበረበት የገጽታ ክፍተት አውጥተው ወደ አዲስ ከፍታ አሸጋግረውታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከተተገበሩት የኮሪደር ልማቶች እስከ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተገነቡት ውብ መዳረሻዎች የዘርፉን ተስፋ ህያው አድርገውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) «እንግዳ ሲመጣ የት እወስደዋለሁ ብዬ አልጨነቅም» ሲሉ የተናገሩት ንግግርም ይህንኑ ነባራዊ እውነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
ቀደም ሲል የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ እንግዳ ሲመጣ የሚጎበኙ ቦታዎች የተወሰኑ እና የነበሩትንም አስተካክሎ የማቅረብ ክፍተት የነበረባቸው ናቸው።
ዛሬ ግን እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአንድነት እና የወዳጅነት ፓርኮች፣ የጎርጎራ፣ ወንጪ እና ጨበራ ጩርጩራ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎቿ ደረጃቸውን የጠበቁ አማራጮችን እንድታቀርብ አድርገዋታል።
ከሁሉም በላይ ግን ይህ አዲስ የቱሪዝም ምዕራፍ ትልቁን በራፍ የከፈተው ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ነው። ቀደም ሲል ቱሪዝም ሲባል ለውጭ ሀገር ዜጎች ብቻ የተተወ ይመስል የነበረውን የተሳሳተ እይታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
ዛሬ ኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ውበትን የሚያደንቁባቸው እና የሀገራቸውን አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በአካል ተገኝተው የሚያዩባቸው በርካታ አማራጮች ተፈጥረውላቸዋል።
የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ማደግ ለዘርፉ የጀርባ አጥንት እና ዘላቂ የገቢ ምንጭ ነው። የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት በተለያዩ ወቅታዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምክንያት ሊቀንስ ቢችል እንኳ፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ዘርፉ ሳይናጋ እና ሳይቀዘቅዝ ዓመቱን በሙሉ ንቁ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርገዋል።
የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት የመሰረተ ልማት እና የቱሪዝም ፕሮጀክቶች የሀገራችንን የተፈጥሮና የታሪክ ሀብት ለዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመጥን እሴት ሰጥተዋቸዋል።
አሁን ላይ ለሀገር መሪዎች ብቻ ሳይሆን ለያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን ከወጭ ሀገር የሚመጡ ወዳጆቻችንም ሆኑ ከየክፍለ ሀገሩ የሚጠይቁን የቅርብ ዘመዶቻችን እና ቤተሰቦቻችን ሲመጡ የት ይዣቸው ልውጣ? የሚለው ጭንቀት አብቅቷል። ይልቁንም ከብዙዎቹ አማራጮች የቱን አስቀድሜ ላሳያቸው? የሚል የደስታ እና የኩራት ምርጫ ውስጥ ገብተናል።
ሁላችንም የሀገራችንን አዳዲስ ውበቶች በመጎብኘት እና እንግዶቻችንን በማስጎብኘት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን እንቀላቀል፤ ኢትዮጵያችንን እንደ አዲስ እንወቅ!
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: