"ሲሾም ያልበላ ... " የሚለው የተሳሳተ ትርክት ለዘመናት የሕዝብን ሀብት ለመዝረፍ ማመካኛ ሆኖ ቆይቷል።
ሹመት እና ኃላፊነት ሕዝብ ማገልገያ ከመሆን ይልቅ፣ የግል ኪስ ማድለቢያ ተደርጎ ይወሰድ የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
አሁን ግን ይህን አጥፊ ዝንባሌ ከስሩ ነቅሎ በመጣል የተቋማትን ንጽህና ለማረጋገጥ እየተወሰደ ያለው ቁርጠኛ እርምጃ ታላቅ ተስፋን ፈንጥቋል።
የመደመር እሳቤን አንግቦ የተነሳው የለውጥ ጉዞ ሌብነትን በሕግ የበላይነት መዶሻ በማድቀቅ በተግባር የሕዝብን አመኔታ የማረጋገጥ ጉዞ ጀምሯል።
ቀደም ባሉት ዓመታት በሕጋዊ ሽፋን በከፍተኛ የመንግሥት መዋቅር ደረጃ ይፈጸም የነበረው መዋቅራዊ ስርቆት የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ ገትቶ ቆይቷል።
እንዲህ ያለውን ሕገ ወጥ መዋቅራዊ መረብ በተቋማት ሪፎርም የመበጣጠሱ ሂደት ከላይኛው የመንግሥት መዋቅር በውጤታማነት ተጀምሯል።
መዋቅራዊ ሌብነትን ለመዋጋት የተጀመረው ይህ ሥራ በፀረ ሙስና ትግል ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ወደ ተቋማዊ ንጽህና የሚደረግ ትልቅ ግግር ነው።
በተቋማዊ ሪፎርሙ ሂደት በየደረጃው በሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ዘንድ የሚስተዋሉ የደላላነት እና የስግብግብነት ዝንባሌዎችን ያለ ምንም ምሕረት ለመታገል ብሔራዊ ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
ትናንት መዋቅራዊ ስርቆትን በማፍረስ የተጀመረው ይህ ትግል ዛሬ በየደረጃው ያሉ ሕገ ወጥ አሠራሮችን እስከ ወዲያኛው ለማስቀረት ጥብቅ ቁጥጥር እና ጠንካራ ተጠያቂነት ወደ ማስፈን ተሸጋግሯል።
የዜጎችን የዕለት ተለት ሕይወት በቀጥታ የሚነኩ ቁልፍ መዋቅሮችን ከሌብነት ማጽዳት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመጠበቅ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ወሳኝ ነው።
ሰሞኑን በልዩ ልዩ ዘርፎች በተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ላይ የተወሰዱ ይፋዊ እርምጃዎች የመንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር አቅም በአግባቡ በጥቅም ላይ እየዋለ ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ነው።
በቁርጠኝነት እየተተገበረ ያለው ይህ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት አፍራሽ አካሄዶችን አስቀድሞ የሚያከሽፍ ጠንካራ ተቋማዊ አሠራር እየዘረጋ ነው።
የሕዝብን አደራ የተቀበለ ማንኛውም የሥራ ኃላፊ ከተጠያቂነት እና ከሕግ ልዕልና ማምለጥ እንደማይችል በተግባር ማሳየት ለነገዋ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ዋስትና ይሰጣል።
የሕዝብ ሀብት የሕዝብ ብቻ ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመረው ብልሹ አሠራርን እና ስግብግብነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞ ውጤታማ ይሆን ዘንድ ከምንም በላይ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ይሻል።
በሐና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: