በቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ተጫዋች አቶ አሸናፊ ግርማ አስተባባሪነት፣ ወደ 120 የሚጠጉ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንን እና ቤተሰቦቻቸውን ያካተተ ልዑክ ዛሬ ከካናዳ ተነሥቶ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ይገኛል።
ልዑኩ ከቶሮንቶ ፒርሰን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲነሳም በካናዳ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ አሸኛኘት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም፣ ይህ ዓይነቱ ጅማሮ የዳያስፖራውን ትውልድ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል እና ማንነት ጋር በማቀራረብ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ልዑኩ በኢትዮጵያ የአንድ ወር ቆይታ የሚያደርግ ሲሆን፣ በቆይታውም ከባህል ልውውጥ እና ከሀገራዊ ትውውቅ ባሻገር በክረምት በጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለማኅበረሰቡ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እንዳደረገ ማወቅ ተችሏል።
ይህ ጅምር በተለይ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ታሪክ፣ ባህልና ማንነት ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተደጋጋሚ ጥሪ መደረጉን አምባሳደር ቴዎድሮስ አስታውሰዋል።
ይህ ጉዞም በኢትዮጵያ እና በዳያስፖራው መካከል የጋራ መግባባት፣ ወዳጅነት እና ትብብርን የሚያጎለብቱ የሕዝብ-ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ድልድዮችን ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑ አንስተዋል።
አምባሳደር ቴዎድሮስ አክለውም እንዲህ ያሉ ጅምሮች የዳያስፖራው ትውልድ ከሀገሩ ጋር ያለውን ትሥሥር ከማጠናከር ባሻገር በሀገር ግንባታ እና በማኅበራዊ ተሳትፎ ያለውን ሚና ለማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የልዑኩ አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ግርማ እና የልዑኩ አባላት በበኩላቸው፣ ይህ ጉዞ ለተሳታፊዎቹ የኢትዮጵያን ባህል እና ታሪክ በቀጥታ ለመለማመድ፣ ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትሥሥር ለማጠናከር እና በበጎ ተግባራት በመሳተፍ ለማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው ይህ ተግባር በቀጣይነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: