Search

የበርሃው ወርቅ፦ ከጉበን አፋፍ የተገኘው የሳሊ ጣፋጭ የህይወት ጉዞ

ዓርብ ነሐሴ 08, 2018 69

በአፋር ክልል በርኃሌ ወረዳ ጉበን ቀበሌ ስንደርስ የበርሃው ንዳድ በአካባቢው የለማው የተፈጥሮ ዕፅዋት አረንጓዴነት ተሸንፏል። የጉበን አፋፍ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች አጊጦ ለዓይን ማራኪ ሆኗል።

በዚህ ውብ የተፈጥሮ ገፅታ ውስጥ ነው አርብቶ አደሩን ሳሊ ሐሰን አሊን ያገኘነው። ሳሊ ከብት በማርባት ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ላይ ይህንን የለማ የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቅሞ ንብ በማነብ አካባቢውን ወደ ማር ምድርነት እየቀየረው ይገኛል።

ቀደም ሲል ከባህላዊ ቀፎዎች የሚያገኘው የማር ምርት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልነበረ የሚያስታውሰው ሳሊ፣ ዛሬ ግን ታሪኩ ተቀይሯል።

በጉዟችን ወቅት በደስታ ተሞልቶ "ይኽው ከግራና ቀኜ እንዲሁም ከጀርባዬ የሚታዩት ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በሙሉ የኔ ናቸው" ሲለን ፊቱ ላይ የሚነበበው የኩራት ስሜት ልዩ ነበር።

ለዚህ አስደናቂ ለውጥ "የችግራችን ሀኪም" በማለት በምስጋና የሚያነሳው በግብርና ሚኒስቴር የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክትን ነው።

ሳሊ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ 10 እስከ 13 ኪሎ ግራም ማር ይቆርጣል። ከአስሩ ቀፎዎቹ በአጠቃላይ እንደየወቅቱ ሁኔታ 80 እስከ 130 ኪሎ ግራም ምርት ይሰበስባል።

የበርሃ ማር በተለይም ከአላይቶ (ቁርቁራ) ከመረካአቶ እና ከሌሎችም ዕፅዋት የሚቀሰመው ማር ለመድኃኒትነት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚፈለግ፣ ምንም ባዕድ ነገር ያልተቀላቀለበት ንጹህ ምርት በመሆኑ በገበያ ላይ ኪሎው እስከ 2,000 ብር ይሸጣል።

"እንጀራውን ቆረስ አድርገን እንደዚህ እንበላዋለን፤ መድሃኒት ነዋ" እያለ ካመረተው ማር እያጣጣመ ያጫወተን አርብቶ አደሩ፣ ኑሮው በጣፋጩ የማር ምርት መለወጡን በፈገግታ መስክሮልናል።

የጉበን ቀበሌ ዛሬ የበርኃሌ የማር ምድር እየተባለች ትጠራለች። ይህ የስኬት ታሪክ ከሳሊም አልፎ ሌሎች አናቢዎችንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

የልማት ፕሮጀክቱ (DRDIP) ምዕራፍ ሁለት፣ ስደተኞችንና የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቡን በማስተሳሰር በማህበራዊና ምጣኔ ሃብት፣ በዘላቂ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ እና በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ እያመጣ ያለው ለውጥ ሀገራዊ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ የሚያግዝ ህያው ማሳያ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: