የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በተለየ ወታደራዊ ጥበብ በፍጥነት ፈጣን ምላሽ ሰጪ አና አስቀድሞ ስጋቶችን መከላከል የሚችል የመከላከያ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ መቺ ኃይል ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻሉ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ስለወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ለሠራዊቱ አመራሮች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ አድርጋ ገና ሳትረጋጋ ባንዳዎች ባደረሱባት ጥቃት ሀገር በተፈተነችበት ወቅት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሠራዊት የተደቀነውን አደጋን በመቀልበስ ረገድ ከባድ የተጋድሎ ትግል አድርገዋል ነው ያሉት።
በዚህም ምክንያት "የውጊያ ማርሽ ቀያሪ የምድር ድሮን" የሚል ስያሜ የተሰጠው የኢትዮጵያ ጠንካራ ክንድ የሕዝቦቿ መተማመኛ ልዩ ኃይል መሆኑን በማብራራት ይህ ዕዝ አስከ አሁን ለሀገር ለከፈለው ዋጋ ኢትዮጵያ እንደምታከብረው እና ነገም ይህንኑ ልዩ ብቃቱን ይዞ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
ሠራዊቱ መሥዋዕትነት የከፈለው እና እየከፈለ የሚገኘው ሀገርን ለማሻገር በመሆኑ ሀገርን ከውጭ ጠላት ከመከላከል ባለፈ፣ የሀገር ውስጥ ሰላምን በማጽናት ሀገራዊ ሕልውናችን ተጠብቆ ዕድገት እንዲቀጥል የሚያስችል፣ የሀገር አንድነት እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የዜጎች ክብር መገለጫ ነው ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
ባንዳ ለሆዱ ሲሞት እኛ ለሀገር ሉዓላዊነት ለሕዝቦች ክብር እና አንድነት እንሞታለን ሲሉም ተናግረዋል።
ሻዕቢያ ከጅምሩ ኢትዮጵያን ከባህር በር ለማራቅ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ፅምዶ ፈጥሮ ኢትዮጵያ ላይ ደባ የሠራ ኃይል ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ህወሓትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሸጠና ለ27 ዓመታት ሥልጣን ይዞ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ አጠንክሮ የሠራ ቅጥረኛ የገዛ ሀገሩን ሠራዊት ያጠቃ የክህደት ኃይል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በህወሓት ክህደት የተፈተነች ነገር ግን ፀንታ የቆመች የልዩ ዘመቻ ሠራዊት መሰል ጠንካራ ዐርበኛ ልጆች ያሏት ሀገር ስለሆነች ጉዞዋን ቀጥላለች ብለዋል።
ፅንፈኞቹን ፋኖን እና ሸኔን ጨምሮ አራቱም የጥፋት ኃይሎች በባዕዳን ስትራቴጂ ሥር ተሰልፈው ኢትዮጵያን የማዳከም እና የማፍረስ ፅምዶ የተባለ ጥምረት ቀርፀው ሕዝባችንን ለስቃይ እና መከራ በመዳረግ ደካማ ኢትዮጵያን ለማየት ጓጉተው ቢሠሩም ይህ ፍላጎታቸው መቼም ሊሳካ እንደማይችል አሳይተናቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመከፋፈል እርስ በእርሱ እንዳይተማመን ያደርግ እንደነበረ አውስተው፣ የትግራይን ሕዝብ ደግሞ የኢትዮጵያ ልጆች እየመጡብህ እና እየከበቡህ ነው እያለ ከወንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ ሲሠራ የኖረ እኩይ ፖለቲካ አራማጅ ፀረ ሀገር ኃይል ነው ብለዋል።
ዛሬ ላይ ያ ሁሉ ሴራ ከሽፎ የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዚህን መሰሪ ቡድን መጥፎ ተግባር በመረዳቱ ወያኔ ከሕዝብ ተነጥሎ መንጠልጠያ ሲያጣ የቀድሞ ጠላቶቹን ሸኔን እና ፅንፈኛ ፋኖን አቅፎ ሻዕቢያን ደግሞ አዝሎ የትላንት ክህደቱን በአደባባይ እየደገመው ይገኛል ብለዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አባላት እነዚህ የጥፋት መልዕክተኞች በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የደቀኑትን ጥፋት በማምከን የጥፋት እግራቸውን በመስበር እብሪታቸውን ማስተንፈስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተለይ የህወሓትን የጃውሳን እና የሸኔን የተላላኪነት ሚና መሰባበር የሻዕቢያን እና የሻዕቢያ ነብስ አባቶችን ተስፋ ማጨለም እንደሆነ በማስረዳት ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ በጀመረችው ዕድገት እና ብልፅግና ወደፊት ትቀጥላለች፤ የታሪካዊ ጠላቶቿ ሕልም አይሳካም፤ የልዩ ዘመቻዎች ጦር ከኢትዮጵያ አያቶች የተቀዳ ዐርበኛ ነው።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በአሁኑ ወቅት በትጥቅም በሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በማስታወስ ለሰፈር ባንዳዎች ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አቅጣጫ በሀገር ላይ ለሚቃጣ ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን እንደዳለበት ማሳሰባቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: