Search

ለጠላቱ የማይጨበጠው ኃያል ሠራዊት

ዓርብ ነሐሴ 08, 2018 82

የአንድ መከላከያ ሠራዊት መዝሙር ተቋማዊ ራዕይን፣ ወታደራዊ ሥነ-ልቦናን እና ብሔራዊ ማንነትን የሚያንፀባርቅ ኃያል የሞራል ግንባታ መሣሪያ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መዝሙር የተቋሙን ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት፣ ታሪካዊ የተጋድሎ ውርስ እና ከሕዝብ ጋር ያለውን ጠንካራ ትስስር ፍጹም በሆነ ውህደት አጣጥሞ ይዟል።

በተለይም በሠራዊቱ ላይ ከተካሄደው ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራ ወዲህ በመዝሙሩ ስንኞች የታተመው ጽኑ ባሕሪ በሠራዊቱ ተጋድሎ እና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በተግባር ጎልቶ ወጥቷል።

"የኩሩ ሕዝቦች መኖሪያ የኅብረብሔር ቡቃያ፤ የሰላም ተምሳሌት ዓርማ የቀለሞች ኅብር ኢትዮጵያ" የሚለው የመዝሙሩ መግቢያ የሠራዊቱን ሕዝባዊ ስብጥር ያብራራል።

ሠራዊታችን በኅበረ ብሔራዊነት የተገነባ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያን ብዝኃነት በአንድነት አስተሳስሮ የያዘ የጽናት መገለጫ ነው።

የሪፎርሙ ውጤት ይህንን ብዝኃነት በማጠናከር ሠራዊቱ የአንድ ቡድን መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ የመላው ሕዝብ መከታ ሆኖ እንዲቆም አስችሎታል።

"ሕዝብ ነው ኃያል ክንዳችን" በሚለው ስንኝ መሠረት ሕዝቡ የሠራዊቱ ዋነኛ ደጀን፣ የኃይል ምንጭ እና የማይነጥፍ የሞራል ስንቅ መሆኑን ያመላክታል።

ይህ ሕዝባዊነት እና ጀግንነት ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጆች በክብር የተመሰከረለት እውነት ነው።

ሠራዊቱ ከሕዝብ የተቀበለውን አደራ በደሙ ለማፅናት መቁረጡን "በደም አሻራሽ አትመው ሕዝቦች ለሰጡን አደራ፤ ለሕገመንግሥቱ ክብር ታጥቀን ቆመናል በጋራ" በሚሉት ስንኞች ይገልጻል።

ሠራዊታችን ከፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ ሆኖ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የመጠበቅ እና ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ የመሆን አደራውን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

የሠራዊቱ የውጊያ ሥነ-ልቦና እና አስቀድሞ የመግታት አቅም "የማንጨበጥ ነበልባል እሳት ነን ለጠላታችን፤ ፍሙ ከርቀት ይፋጃል ብረት ያቀልጣል ክንዳችን" በሚሉት ኃያል ስንኞች ይገለጻል።

ይህ የጀግንነት ባሕሪ ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታጅቦ ጦርነትን ሳይጀመር የመቋጨት ስትራቴጂካዊ ልቀት ላይ ደርሷል። "ፍሙ ከርቀት ይፋጃል" የሚለው ሀሳብ ዛሬ በተግባር ተተርጉሟል፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊ 4 ትውልድ ተዋጊ ጄቶችን በመታጠቅ እንዲሁም ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚጠቀሙ ዘመናዊ ድሮኖችን በማሰማራት የጠላት ግቦችን በከፍተኛ ትክክለኛነት ሲመታ የጀግንነቱ ክንድ ከርቀት መፋጀቱን አረጋግጧል።

ይህ የማይበገር ኃይል የጠላቶችን የጦርነት ዕቅድ እና የጂኦ-ፖለቲካ ስሌት ሙሉ በሙሉ በማናጋት በፈሪ ዛቻ እና ተስፋ በቆረጠ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ ብቻ እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል።

ሌላው የሠራዊቱ ጀግንነት መገለጫ የሆነው የተዘረጋው የሳይበር አቅም እና ለሠራዊቱ የሚያስፈልጉትን ዘመናዊ መሳሪያዎች በራስ አቅም የሚያመርተው የመከላከያ ኢንዱስትሪ የዚሁ "ብረት አቅላጭ" ክንድ ማሳያዎች ናቸው።

የዚህ ሁሉ የጀግንነት እና የኃይል መግለጫ ዓላማ ጦርነትን መፈለግ ሳይሆን ሰላም እና ልማትን ማስፈን መሆኑ "ሰላም ልማት ነው ቋንቋችን፤ የመፈቃቀድ አንድነት እኩልነት ነው ዜማችን" በሚለው ስንኝ በግልጽ ተሰምሮበታል።

ዛሬ በምድር ጦር፣ በአየር ኃይል፣ በድሮን ቴክኖሎጂ፣ በሳይበር እና በኮማንዶ ኃይል መካከል የተፈጠረው ፍጹም የጋራ ቅንጅት፣ እንዲሁም ሰፊው ሕዝባዊ መሠረት የኢትዮጵያን ደጀንነት አጽንቷል።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ እና በዘመናዊ መከላከያዋ ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: