ውኃ ዝም ብሎ ፈሳሽ አይደለም፣ ውኃ ቅኔ ነው፤ ጥልቅ ምሥጢር እና የማይተካ የሕይወት እስትንፋስ ነው። ዛሬ በዓለማችን ላይ "ፈሳሽ ወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ይህ ውድ ሀብት፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዋነኛ የጂኦ-ፖለቲካ የጦር አውድማ ሆኗል።
የዚህች "ሰማያዊ ፕላኔት" 99 በመቶ ውኃ ጨዋማ እና በበረዶ የተያዘ ሲሆን፣ የሰው ልጅ ሕልውና የተንጠለጠለው በ1 በመቶ ንጹሕ ውኃ ላይ ብቻ ነው።
በዚህች ጠባብ መቶኛ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት የውኃ ሀብት ለዘመናት የበረከት ምንጭ ከመሆን ይልቅ፣ የረቀቀ እና የተደራጀ የውጭ ሴራ ማጠንጠኛ ሆኖ ኖሯል።
ታሪክ ጸሐፊው ሄሮዶተስ "ግብጽ የናይል ስጦታ ናት" ብሎ ከተናገረበት ዘመን ጀምሮ፣ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የውኃውን ምንጭ ለመቆጣጠር ያልሸረቡት ሴራ የለም።
ከ150 ዓመታት በፊት እንግሊዞች እና ፈረንሳዮች የናይልን ተፋሰስ ለመቆጣጠር ባደረጉት ሽኩቻ ወቅት አንድ አስገራሚ የፖለቲካ ዶክትሪን ተቀርጾ ነበር፦ "በላይኛው የውኃ ተፋሰስ (ኢትዮጵያ) ላይ የነቃ እና የሠለጠነ ኃይል ከኖረ ግብጽ አለቀላት፤ ስለዚህ ይህ ኃይል በተለያዩ ስልቶች መዳከም፣ በእጅ አዙር መመታት እና ዘላለሙን በድኅነት መኖር አለበት።" የሚል።
ይህ የቅኝ ገዥዎች ዶክትሪን ዛሬም ድረስ ሳይቀየር ኢትዮጵያን ለማተራመስ በሚተገበር የሴራ መረብ ውስጥ ጉልህ ሆኖ ይታያል። ዓላማው አንድ እና አንድ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ዘወትር እርስ በርስ እንዲናከሱ በማድረግ ሀብታቸውን ለማልማት ጊዜ እና አቅም እንዳያገኙ ማድረግ ነው።
ይህ ሴራ በዓባይ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። የኢትዮጵያን የውኃ ፖለቲካ ስንመረምር፣ ባሮ አኮቦን እና ተከዜን መዘንጋት አንችልም። በተለይም የባሮ አኮቦ ሶባት ተፋሰስ፣ የኢትዮጵያን 27 በመቶ ለመስኖ ምቹ መሬት ያቀፈ እና ከፍተኛ የውኃ መጠን ያለው ግዙፍ ሀብት ነው። ሆኖም ጋምቤላ፣ የእንግሊዝ ፖለቲካ መናገሻ ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ ዛሬ ድረስ፣ የውጭ ኃይሎች በድብቅ የሚራወጡባት፣ የኮንትሮባንድ ንግድ የሚያብብባት፣ እና የደቡብ ሱዳንን አለመረጋጋት ሰበብ በማድረግ በተዘዋዋሪ የምትታመስበት ቀጠና ሆናለች።
በቀድሞ ዘመን እንግሊዞች ጋምቤላ ላይ ወደብ መሥርተው የኢትዮጵያን ቡና በባሮ ወንዝ በኩል በማስወጣት በጀልባ ወደ አውሮፓ ካፌዎች ያስገቡ ነበር። ዛሬም ያ ስትራቴጂያዊ ቀጣና ከእጃችን ወጥቶ የውጥረት ማዕከል እንዲሆን ይፈለጋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በሱዳን በኩል የሚደረገው ጥቃት፣ ዒላማው የተከዜን እና የአትባራን የውኃ ጥላ ለመያዝ፣ እንዲሁም የሁመራ እና የወልቃይትን ለም የመስኖ መሬቶች ከኢትዮጵያ ነጥቆ የውኃ የበላይነትን ለማረጋገጥ መሆኑን መረዳት አያዳግትም።
በዚህ የውኃ ፖለቲካ መሐል፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬም በባሕር ውስጥ "እየዋኘን" ነው። አዎ! ኃያላን አዞዎች እና ዓሣ ነባሪዎች በሞሉበት ማዕበላማ የፖለቲካ ባሕር ውስጥ ሀገራችንን በጀርባችን አዝለን እየዋኘን ነው። መዋኘት ስንጀምር፣ ግድብ ሠርተን ከድኅነት ልንወጣ ስንታገል፣ የተኙት አዞዎች ነቁ።
ዛሬ በየአካባቢው የምናየው ታጣቂ ማደራጀት፣ ሰርጎ ገቦችን የማሰማራት ድርጊት፣ እንዲሁም አርቲፊሻል ግጭቶች በዘፈቀደ የመጡ አጋጣሚዎች አይደሉም። ከጀርባቸው፣ የውኃ ሀብታችንን በብቸኝነት ለመቆጣጠር የሚፈልጉ፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተባልተው አቅም እንዲያጡ የሚሠሩ የውጭ ኃይሎች እና የእነሡ የውስጥ ተላላኪዎች አሉ።
ዛሬ ጦርነት መልኩን ቀይሯል፤ ሠራዊት ከማዝመት ይልቅ፣ የሀገር ውስጥ ባንዳን ማስታጠቅ፣ የኢኮኖሚ ሳቦታጅ ለመፍጠር በተልእኮ መሥራት፣ ሕዝብን በስስ ስሜቱ ማጋጨት ዋነኛ መሣሪያቸው ሆኗም።
ስለዚህ፣ ከዚህ አደገኛ የእንቅልፍ አዙሪት ልንነቃ ይገባል። የንብ ቀፎ ነክቶ መተኛት እንደማይቻለው ሁሉ፣ የውኃ ሀብታችንን ለማልማት ተነስተን መዘናጋት ታሪካዊ ዋጋ ያስከፍለናል።
እኛ የጀመርነው ትግል የሕልውና ትግል ነው። ጠላቶቻችንን የምናሸንፈው፣ ይህንን የተደራጀ እና የዘመናት ሴራ በውል ተረድተን፣ ከልዩነቶቻችን በላይ ሀገራዊ ሕልውናችንን አስቀድመን ስንተባበር ብቻ ነው።
አዞዎቹን በጀግንነት ተጋፍጠን፣ የተሸከምናትን ሀገራችንን አረንጓዴው መስክ ላይ በሰላም እስክናቆማት ድረስ፣ መዘናጋት እና እንቅልፍ ለእኛ እርም ነው! ነቅተን ፈሳሽ ወርቃችንን እናድን!
ኢትዮጵያ ትናንት ይህንን ሴራ በመበታተን የሕዳሴ ግድቡን አሳክታለች። የእነዚህን ጠላቶች ሴራ በማክሸፍ ባንዳዎችን በማሸነፍ ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ወደ ቀይ ባሕር ወደ ሁለተኛው የውኃ አካላችን ለመድረስ የምናደርገውን ጥረት እንቀጥላለን!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: