Search

ከታሪክ ስብራት ወደጋራ ከፍታ፡ የነገዋን ኢትዮጵያ የምንቀርጽበት የምክክር ጉባኤያችን

ዓርብ ነሐሴ 08, 2018 45

ለዘመናት ኢትዮጵያን ሲፈትኑ የቆዩ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የተጀመረው ታሪካዊ ምክክር የማጠቃለያ ጉባኤ እንደቀጠለ ነው።

ከሐምሌ 8 ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፣ ልዩነቶችን አብላልቶ ወደ ጋራ መግባባት በመሸጋገር በውሳኔ ማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ይህ የምክክር ሂደት በፖለቲካው ምኅዳር ጫፍ ላይ የነበሩ አመለካከቶች የጋራ ቤታችን የሆነችው የኢትዮጵያ ጉዳይ የሁላችንም ነው በሚል እሳቤ ወደ ወደ ውይይት ጠረጴዛ መጥተው ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሸሩ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።

ይህ አካሄድ የፖለቲካ ገበያውን ከብጥብጥና ከአፍራሽ እንቅስቃሴ አውጥቶ በሰከነ ሀሳብ ላይ እንዲመሠረት ታላቅ አቅም ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ከሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች እና ከዳያስፖራው የተወከሉ 4 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን በአንድ መድረክ ተሰብስበው ሀገራዊ ራዕይን ማዕከል ባደረጉ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው።

የውይይቱ መዋቅራዊ ሂደትም ከትንንሽ ቡድኖች ተነስቶ እያንዳንዳቸው 500 አባላት ወዳሏቸው 8 ዓበይት ቡድኖች ያደገ ነው።

እነዚህ ቡድኖች በሰላም ግንባታ፣ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሀገርና በተቋማት ግንባታ፣ በሕግ የበላይነት እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስትራቴጂዎች ዙሪያ በሰከነ መንፈስ ሲመክሩ ቆይተው፣ በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ሥራቸውን በተሳካ ሁኔታ እያጠናቀቁ ነው።

አሁን ባለው ወሳኝ ምዕራፍ የተበታተኑ ምክረ ሀሳቦችን ወጥነት ባለው መልኩ ለማደራጀትና ለማጣጣም ከተለያዩ ቡድኖች የተዋቀሩ ልዩ ቡድኖች ሥራቸውን ጀምረዋል።

የምክክር ሂደቱ ውሳኔ አስተላላፊ ሳይሆን ለሚመለከተው አካል ግብዓት የሚሆኑ የበሰሉ ምክረ ሀሳቦችን የሚያቀርብ በመሆኑ፣ በርካታ አጀንዳዎች ወደ ልማትና ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ስትራቴጂነት እየተቀየሩ ይገኛሉ።

በሂደቱ ለሚነሱ ማናቸውም ቅሬታዎችም ግልጽ የሆነ የመፍቻ አሠራር የተዘረጋ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሂደቱ 3/4 ሥራውን በማጠናቀቁ፣ የመጨረሻው ውጤት በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

በጋራ ርብርብ እውን እንደሆኑት ደማቁ የዓድዋ ድል እና ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁሉ፣ ይህ የምክክር ሂደትም በውይይትና በመደማመጥ ታሪክ የመፃፊያ ሌላኛው አኩሪ ሀገራዊ ዐሻራ ሆኖ በኩራት ይመዘገባል።

ተመካካሪዎች በጋራ ያዘጋጇቸው ምክረ ሀሳቦች ነገን የምታሻግር፣ የፀናችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የማይናወጥ ጽኑ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: