Search

የግብጽ ሚዲያዎች ስለ ሕዳሴ ግድብ ከራሳቸው ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር የሚቃረን ዘገባ እያቀረቡ ነው፦ ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ዛሂድ ዚዳን

ዓርብ ነሐሴ 08, 2018 63

የግብጽ ሚዲያዎች ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ወጥነት የሌላቸው እና ከበርካታ የግብጽ ሳይንቲስቶች እና የውኃ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ግምገማዎች ጋር የሚጋጩ መሆናቸውን ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ዛሂድ ዚዳን ገለጹ።

አስተያየታቸውን የሰጡት ዛሂድ፤ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ክርክሮች በሳይንሳዊ እና ቴክኒካዊ ትንተናዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ አሻሚ እና እርስ በርስ በሚቃረኑ የመገናኛ ብዙኃን ተረኮች የሚመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የግብጽ የጂኦሎጂ ባለሙያ ዶክተር አባስ ሸራቂ ግድቡ በተፈጥሮው በግብጽ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርስ በግልጽ ካስረዱት የሀገሪቱ ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ ጋዜጠኛው ጠቅሰዋል።

ሌላኛው የግብጽ ሳይንቲስት ዶክተር ሳመህ አርማኒዮስ፤ ሕዳሴ ግድብ በወንዙ ፍሰት ላይ ምንም ዓይነት የውኃ እጥረት ሳይፈጥር ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ውኃው በቀጥታ ወደ ወንዙ የሚመለስበት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት መሆኑን ማብራራታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የሕዋ ሳይንቲስቱ ዶክተር ፋሩክ ኤል-ባዝ ግድቡ የተሻለ የውኃ አስተዳደር እንዲኖር በማድረግ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የሱዳንን እና የግብጽንም ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ማመልከታቸውን ዛሂድ አብራርተዋል።

ጋዜጠኛው እንደ ፕሮፌሰር ሰይፍ አል-ዲን ሀማድ እና የቀድሞ የሱዳን የውኃ እና መስኖ ሚኒስትር ኡስማን አል-ቶም ያሉ የሱዳን ባለሙያዎችን በመጥቀስ፣ ስለ ዓባይ ወንዝ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ በፖለቲካዊ ጩኸት ሳይሆን በሳይንሳዊ እና በተረጋገጡ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ትንተና ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

አንዳንድ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ግድቡን በአንድ ወቅት ከጎርፍ እና የመሠረተ ልማት ውድመት ጋር በማያያዝ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ የውኃ መጠን መቀነስ እና ድርቅ ያስከትላል በማለት የሚከሱበት መንገድ ፍጹም የሚቃረን ሐሳብ ነው ብለዋል።

ዛሂድ አክለው እንደገለጹት፣ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ አደጋ ይደቅናል የሚሉ የፖለቲከኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ውንጀላዎች ፖለቲካዊ ፍላጎትን ያዘሉ እንጂ ወጥ የሆነ ሳይንሳዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው።

ይህ ዓይነቱ የተሳሳተ ትርክት ኢትዮጵያ ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ከሚፈስሰው የናይል ውኃ 86 በመቶ ድርሻ ካለው ከዓባይ ወንዝ የተፈጥሮ ሀብቷ የመልማት መብቷን ለማደናቀፍ ለበርካታ ዐሥርታት ሲከናወን የቆየ አካሄድ እንደሆነም ነው ያስረዱት።

አጠቃላይ የዓባይ ወንዝ ዓመታዊ የውኃ መጠን በክረምቱ ወራት ወዲያው ሊታወቅ የሚችል ባለመሆኑ፣ ስለ ውኃው መጠን ቀድሞ ድምዳሜ መስጠት አይቻልም ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ይልቁንም የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ከፖለቲካዊ ጩኸት በመውጣት በሳይንሳዊ ጥናቶች እና በተረጋገጡ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ሚዛናዊ ዘገባ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: