በዓለም አቀፍ ደረጃ "White-Collar Crime" (የክራባት ለባሽ ሌብነት) በመባል የሚታወቀው ጽንሰ-ሐሳብ፣ ከፍተኛ የሕዝብ አገልጋይነት አደራን እና ሙያዊ ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው፣ በስልጣን፣ በዕውቀት እና በኃላፊነት ሽፋን የሚፈጸም ረቂቅ የሙስና ተግባር ነው።
ይህ ጽንሰ-ሐሳብ በሥነ-ወንጀል ጥናት ሲዳብር፣ መጀመሪያ ላይ የሚያተኩረው በትላልቅ የንግድ ተቋማት ውስጥ በሚፈጸም የገንዘብ ማጭበርበር ላይ የነበረ ቢሆንም፣ ከጊዜ በኋላ ግን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች ጋር በትስስር የሕዝብን ሀብት በህጋዊነት ሽፋን የሚመዘበርበትን ሂደት የሚገልጽ ሆኗል።
ወንጀሉ በጉልበት፣ በጦር መሳሪያ ወይም በአመጽ የሚፈጸም ሳይሆን፣ በብዕር፣ በፊርማ፣ በኮምፒዩተር፣ በሚዲያ አጀብ ጭምር አንዳንድ ጊዜ የሚሸፈን በጭብጨባ የታጀበ እና በስልጣን ወንበር ላይ በሚቀመጡ፣ ታላላቅ የንግድ ተቋማትን ባቋቋሙ እና በማህበረሰቡ ክብርና እምነት በሚሰጣቸው አካላት የሚከወን ነው።
የክራባት ለባሽ ሌብነት በባህሪው እጅግ አሳሳች፣ ውስብስብ እና አደገኛ ነው። አፈጻጸሙም ንግግሩም ጸአዳ፣ አንደበቱ ሌብነትን አምርሮ የሚጠየፍ፣ በሕዝብ ስም የሚምል እና ለሀገር የቆመ የሚመስል፤ በአለባበሱም ሆነ በአቀራረቡ እጅግ ማራኪ ሆኖ ሳለ፣ በተግባር ግን የቆሸሸ እና የሕዝብን ሀብት በስልታዊ መንገድ የሚበዘብዝ ግፍ አስደንጋጭ የሌብነት መረብ ሚዘረጋበት ነው። እነዚህ አካላት ውጫዊ ገጽታቸውን አሳምረው፣ ውስጣዊ ማንነታቸውን በህገ-ወጥ የጥቅም ትስስር ያጠቆሩ፣ የሕዝብን አደራ ለግል ብልጽግናቸው የሚለውጡ ናቸው።
ይህ የክራባት ለባሽ ሌብነት እያደገ ሲሄድ በአንዳንድ ሀገራት እንደታየው መንግሥትን እጅ ወደ መጠምዘዝ ሲሄድ ታይቷል፡። በተለይ ሌብነትን ለመቆጣጠር ቁርጠኛ አቋም በሌላቸው መንግሥታት ውስጥ ወደ ስቴት ካፕቸር ደረጃ ሊያድግ የሚችልበት በር ክፍት ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ገና ጅምሩ ሌብነትን ለመዋጋት መንግሥታዊ ቁርጠኝነቱ ከፍተኛ ሆኖ መታየቱና ሌብነትን ከንግግር በዘለለ ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ በመነደፉ ምክንያት ጠንካራ ልማትን የሚያረጋግጥና ያቀደውን የሚፈፅም መንግሥት እንዲኖር አስችሏል፡፡
ለዚህም ነው ሌብነት ሀገራዊ ሥርዓቱን ጠምዝዞ ለመያዝ አልቻለም። ይህ እጅግ መሰረታዊ እና ሊሰመርበት የሚገባ ትልቅ ሀገራዊ እውነት ነው። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተገነባው ሥርዓት በሙስና አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀ፣ በሌቦች የተጠመዘዘ እና አቅም ያጣ ሳይሆን፣ ታላላቅ ሀገራዊ ልማቶችን በብቃት ማስፈጸም የሚችል እጅግ ጠንካራ መንግሥታዊ ቁመና ያለው ነው።
መንግሥት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት ከማስፈጸም ባሻገር፣ ለሕዝብ የሚጠቅም ሀብትን በከፍተኛ ቁጠባ ማሰባሰብ የሚችልበትን የተቋማዊ አቅም ደረጃ አዳብሯል። ከዚህም በላይ፣ የሕዝብን ሀብት የሚውጡ የሙስና ቀዳዳዎችን የሚያጸዳ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ (Digitalization) እና ግልጽነትን የተላበሰ የመንግሥት መዋቅር ተፈጥሯል። እዛም እዚህም በሚታዩ በክራባት ለባሾች አሻጥር ሳይበገር፣ ትላልቅ ሀገራዊ ራዕዮችን ወደ መሬት በማውረድ ላይ ይገኛል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ከዚህ የክራባት ለባሽ ሌብነት ፈተና በድል እየወጣች መሆኗን በተግባር እያረጋገጠች ነው። ይህ የሆነው በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ዕውን የሆነው የመደመር መንግሥት በፍጥረቱ ሌብነት ጠል መንግሥት መሆኑ ነው፡፡
ሀገራችን በፈጣን ልማቷ፣ በግብርናው ዘርፍ ባስመዘገበችው ስኬት እና በሚታዩት ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ሥራዎቿ ብቻ ሳይሆን የምትገለጸው፣ ይህንን ልማት ከሚፈታተኑ የውስጥ ሌቦች ጋር በምታደርገው የማያወላውል እና ቆራጥ ትግል ጭምር ነው።
የሕዝብ አገልጋይ መስለው ሕዝብን የሚበዘብዙ፣ በአንደበታቸው እያባበሉ በተግባር ሀገርን የሚዘርፉ አካላትን በቴክኖሎጂ እና በህግ አግባብ ከሥርዓቱ ውስጥ በማውጣት ተጠያቂነትን በማስፈኗ፣ ኢትዮጵያ በክራባት ለባሽ ሌብነት ላይ ትልቅ ፖለቲካዊ ድል ተቀዳጅታለች።
ይህ ታሪካዊ ፖለቲካዊ ድል የተገኘው መንግሥት ተቋማዊ ግልጽነትን በማስፈን እና የተጠያቂነት እርምጃዎችን በማጠናከሩ ነው። የክራባት ለባሽ ሌብነትን እውነተኛ ገጽታ በማጋለጥ፣ አንደበትን ሳይሆን፣ ተግባርን የሚመዝን ጠንካራ የህግ የበላይነት ሥርዓት በተግባር አሳይቷል።
በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ የሕዝብን አደራ በበሉ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ፣ ልማቷን በማፋጠን እና ሥርዓቷን ከሌቦች በማጽዳት፣ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በአሸናፊነት እየቀጠለች መሆኗን ይህ ውጤት በግልጽ ያሳያል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: