Search

ትውልድ የበላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፈተና እና አዲሱ የተስፋ ብርሃን

ሓሙስ ነሐሴ 07, 2018 83

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሀሳብ አልባ የበቀል ፖለቲካ ከሆነ ውሎ አድሯል የሚሉ ወገኖች፣ ምናልባትም የአንድ ትውልድ ሂደትን በአንክሮ የተመለከቱ ናቸው።

ይህ ሀሳብ አልባ ፖለቲካ ደግሞ ጽንፈኝነትን ወልዶ ከአንድም ሁለት ትውልድ ስለመብላቱ ዛሬም አብረውን ሆነው የሚመክሩን አልጠፉም።

በሃምሳዎቹ እና ስልሳዎቹ የጀመረው "የእኔ ሀሳብ ብቻ ምርጥ ነው" አካሄድ፣ "አንባቢ ትውልድ ነኝ" ብሎ ሲያስብ በነበረው ወጣት እንኳን ሲያቀነቅነው በነበረው ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ሳያስማማ ለሀገር የሚጠቅም አንድ ሙሉ ትውልድ በልቶ አልፏል።

"እናሸንፋለን" እና "እናቸንፋለን" በሚሉ የመሳሰሉ ታሪካዊ ስህተቶች ያገዳደለው ትውልድ በከተማ ጦር ተመዝዞ ተገዳድሎ፣ የከተማ ጦርነቱ አላዋጣ ሲል ወደ ጫካ አምርቶ በዚያም በርካቶችን የጥይት እራት አድርጎ የሴራ ድር ማድራቱን ቀጠለ።

ያ ከከተማ እስከ ጫካ የቀጠለው በአንድ ዓላማ ሥር ተሰልፈው ሃሳብ ለማንሸራሸር የፈለጉትን ግማሹን በልቶ ሌሎቹን ማሰደዱን ለማየት ብዙ መጽሐፍ ማገላበጥ የሚጠይቅ አይደለም። ይልቁንም በጫካ እያለ በአንድ ሌሊት የፈጃቸው እና በተአምር ሕይወታቸው ተርፎ በስደት የኖሩት ፖለቲከኞች ለዚህ ምስክሮች ናቸው።

በእርግጥ ፖለቲከኛ ማነው? ብሎ ለሚጠይቅ ሰው መልስ መስጠት በሚቸግርበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሴራ ያለፈ መግደል እና መገዳደል መለያው እስኪመስል ብዙ ዓመታትን ተጉዘንበታል።

እንዲህም ሆኖ የበላውን በልቶ ያጠፋውን አጥፍቶ በኢትዮጵያውያን መቃብር ላይ የተመሰረተው መንግሥት የነበረውን ተስፋ ሳይሆን ሌላ የሀገር መከራን አዋልዶ፣ በ17 ዓመታት ሺህ ወጣቶችን በልቶ ጥቂቶችን ወደ ሥልጣን ቢያመጣም የሃሳብ ልዕልናን ማምጣት ግን አልቻለም።

አሁንም ተስፋ ይመጣል ብለው ይጠብቁ የነበሩትን ተስፋ አሳጥቶ እሱም ተጠናቆ ሌላ የ27 ዓመታት ሴራን ተክቶ የለመደውን ትውልድ የመብላት መንገድ ይዞ ተጉዟል።

"የእኔ ብቻ ሃሳብ ምርጥ ነው" የሚለው አካሄድ ጽንፈኝነት ወልዶ ሌሎች ጫካ ናፋቂዎችን አፍርቶ ሀገርን ፈተና ውስጥ እንድትቆይ አስገድዷታል።

ዛሬ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጽንፈኝነትን ፈልፍሎ ሕዝብ መከራውን እንዲገፋ እያደረገ ያለው ችግር የተወለደው፣ ከዚህ ከረጅም ጊዜ የ”እኔ አውቅልሃለሁ” ጸረ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ ነው።

ዓለም ወደ አምስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት እየተሸጋገረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ በአዳራሽ ውይይት ሊፈቱ የሚችሉ የፖለቲካ ልዩነቶች ሁሉ ጠመንጃ አስነክሰው ወደ ጫካ የሚያስሮጠው ይኸው ልክፍት ነው።

ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት፣ የሕዝብ ተቋማትን በማውደም፣ በሃሳብ ልዩነት ሰዎችን መፈረጅ እና ማሰቃየት፣ ከባዳ ጋር ተባብሮ በባንዳ ሀገርን መውጋት፣ በአመጽ የፈረሱ ሀገራትን እንደምሳሌ በማንሳት ያንን መንገድ ለሀገር መመኘት እና ሌሎች ጽንፍ የረገጡ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የ"እኔ ብቻ ትክክል ነኝ" አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው።

"የመደመር መንግሥት" መጽሐፍ እንደሚያስቀምጠው፤ የሌሎችን እውነታ፣ ሁኔታና አመለካከት ወደ ራስ ወስዶ ለመመልከትና ትኩረት ለመስጠት አለመቻል ወይም አለመፍቀድ፤ ሌሎች አማራጮችን ለመቀበል አለመፈለግ፤ ሁልጊዜ ‘እኔ ያሰብኩት፣ እኔ የያዝኩትና እኔ ያመንኩት ብቻ ልክ ነው’ ብሎ ማመን የዚህ ግትርነት ማሳያ ነው።

"ከእኔ ጋር ካልሆነ ከጠላቴ ጋር ነው" ብሎ መፈረጅ፣ አደገኛውን እና የመጨረሻውን ደረጃ ደግሞ፤ የአመለካከት ወይም የአስተሳሰብ ጽንፍን በቀጥታ ወደ ተግባር መቀየር እንደሆነም በመጽሐፉ ተገልጿል። ይህ ደግሞ በፖለቲካ ገበያ ውስጥ ቡድኖች የግል እና የቡድን ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ጽንፈኝነትን መመርኮዣቸው ማድረጋቸውን ያሳያል።

በአንድ ቡድን ያሉ ግለሰቦች በተናጠል ከሚኖራቸው የጽንፈኝነት አዝማሚያ ይልቅ ቡድኑ በድምር የያዘው የጽንፈኝነት አዝማሚያ እጅግ አደገኛ ነው። እነዚህ በቡድን የሚሰባሰቡ አካላት ቡድናቸውን በመርሕ፣ በአመክንዮ እና በዴሞክራሲ ከመመሥረት ይልቅ፣ ለሌሎች ቡድኖች ባለ ጥላቻ፣ ተቃርኖ እና ትግል እየመገቡ ያቆዩታል።

"ብዙ ሰው አለ፤ ሐሳቡ የብዙዎች ነው፤ እኔ ብቻዬን አላጠፋሁም፤ ችግር ከመጣ በጋራ እንጠየቃለን" የሚሉ ስሜቶች እና ጽንፈኝነት በቡድን ውስጥ እንዲጸና እና ግለሰቦች ከተጠያቂነት እንዲሸሹ ያደርጋሉ።

እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች ናቸው ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሱ በዚህ ሰዓት የእምነት ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን እና ሌሎች ሕዝባዊ ተቋማትን ሳይለይ እየፈተኑ ኢትዮጵያንም ዋጋ እያስከፈሉ ያሉት።

ሆኖም ይህንን የዘመናት የታሪክ እና የፖለቲካ ስብራት ለመፍታት፣ እንዲሁም የተበጣጠሰውን ማህበራዊ ትስስር ለመጠገን አሁን ላይ በአዲስ ምዕራፍ የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት እጅግ ትልቅ ተስፋን ሰንቋል።

ይህ አካታች አገራዊ የምክክር መድረክ ያንን አሮጌውን የመጠፋፋት እና ትውልድ የመበላላት መንገድ ለዘለቄታው ዘግቶ፣ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ የመፍታት እና አዲስ የመነጋገር ባህልን የሚፈጥር ብሩህ የጋራ መንገዳችን ነው።

የ"እኔ ብቻ ልክ ነኝ" ፖለቲካን ትተን፣ ሀገር የምትድነው በ"እኛ" ጽኑ አንድነት እና በሰለጠነ ምክክር መሆኑን በተግባር የምናሳይበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

በጌቱ ላቀው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: