የአንድ ሀገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደኅንነት በጽኑ መሠረት ላይ ሊቆም የሚችለው ድንበርን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ዘመናዊና ጠንካራ ተቋም ሲገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ማንነት አቅፎ በመያዝ "ትንሿ ኢትዮጵያ" ተብሎ የሚጠራው ይህ አንጋፋ የወል ቤታችን፣ የሀገር ውስጥና የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የማይተካ ሀገራዊ ሚናውን በብቃት እየተወጣ ነው።
በቅርቡ ሠራዊቱ በአስተሳሰብ፣ በመዋቅርና በማድረግ አቅም ላይ ባደረጋቸው ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች የላቀ የጦር ጥበብና ወታደራዊ ዕውቀት ባለቤት መሆን ችሏል።
በተለይም ልዩ ወታደራዊ ጥበብ ያለው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ መገንባቱ፣ ከውስጥና ከውጭ የሚቃጡ የጥፋት ተልዕኮዎችን አስቀድሞ በማምከን ሠራዊቱን ወታደራዊ ማርሽ ቀያሪ አቅም አጎናጽፎታል።
የሠራዊቱ ግዳጅ በጦር ሜዳ ውጊያ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በሰላም ጊዜ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጣን አጋዥ በመሆን፣ የአርሶ አደሩን ሰብል በመሰብሰብ እንዲሁም የኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ የልማትና የአንድነት ትልቅ ዋስትና መሆኑን አረጋግጧል።
ከሀገር ወሰን በተሻገረ መልኩም በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ በተሰማራባቸው ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ባሳየው ከፍተኛ ዲስፕሊንና ጀግንነት የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የማንንም ሀገር የማይወር፣ ነገር ግን የሀገርን ክብርና ዳር ድንበር ለመጠበቅ ማንኛውንም መስዋዕትነት የሚከፍል የህዝብ አለኝታ ነው።
በመሆኑም ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና ልማት እንዲፋጠን ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጠውን ይህንን ጀግና ሠራዊት ማጠናከር፣ ማክበርና ከጎኑ መቆም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ግዴታ ነው።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: