Search

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትናንት እስከ ዛሬ ታላቅነት - የትውልድ ቅብብሎሽ

ቅዳሜ ነሐሴ 09, 2018 74

የመደመር ፍልስፍና የትናንትን በጎ ታሪክ ሳያፈርሱ፣ ዘመናት ያወረሱንን ሥርዓታዊ ጉድለቶች እያረሙ፣ የዛሬን ዐቅም አሰባስቦ ነገን በተሻለ መሠረት ላይ የመገንባት ጥልቅ የሐሳብ ዘር ነው። ይህ የሐሳብ ዘር ወደ መሬት ወርዶ እጅግ አስደናቂ የተግባር ፍሬ ካፈራባቸው አንኳር ሀገራዊ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ከትናንት እስከ ዛሬ የተዘረጋውን የትውልዶች የጀግንነት ወኔ፣ ሀገር ወዳድነትና የአርበኝነት መንፈስ በክብር የተረከበና ተቋማዊ አቅሙን ወደ አዲስ የልቀት ማማ ያሻገረ አንጸባራቂ ተቋም ሆኖ ቆሟል።

ዘመናዊው የኢትዮጵያ ሠራዊት ሥረ-መሠረት ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሲዋቀር፣ ሠራዊቱ የውጭ ወራሪዎችን በማንበርከክ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የኩራት ምንጭ የሆነውን አንጸባራቂውን የዓድዋን ድል አስመዝግቧል። ይህ በዱር በገደሉ የተዋጋውና ለሀገሩ ነፃነት አጥንትና ደሙን የገበረው ሠራዊት፣ ከ40 ዓመት በኋላ የተመለሰውን ፋሺስት ጣሊያንን በጀግንነት ከመፋለም አልፎ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመንም ሆነ በደርግ ሥርዓት የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባሕር በር እና የባሕር ኃይል ሉዓላዊነትን በንቃት ሲጠብቅ የኖረ የሀገር መከታ ነው።

ቆየት ብሎም የዚያድ ባሬን ወራሪ ኃይል ድባቅ በመምታት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ያስከበረው ይኸው ከአባቶቹ የወረሰውን የጀግንነት እና ሀገር ወዳድነት መንፈስ የተላበሰው ቆራጡ የሠራዊት አባል ነው። ይህ ታሪክ ሠራዊቱ ለሀገሩ ዳር ድንበር መከበር ምን ያህል መሥዋዕትነት ከፋይ እንደነበረ አጉልቶ ያሳያል።

ይሁን እንጂ፣ ሠራዊቱ በጀግንነትና በሀገር ፍቅር ወደር ያልተገኘለት ቢሆንም፣ በየዘመናቱ የነበሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች የሠራዊቱን ታማኝነት ለሀገርና ለሕዝብ ከማድረግ ይልቅ፣ ለራሳቸው ፖለቲካዊ ሥርዓትና ርዕዮተ ዓለም ጠባቂነት ሲያውሉት ቆይተዋል።  ከዚህም የከፋው ታሪካዊ ስብራት ደግሞ፣ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የነበረውን ሀገር ጠባቂ ሠራዊት "የደርግ ሠራዊት ነው" በሚል ፈርጆ ያለምንም ርኅራኄ መበተኑ ነው።

የሀገር ዳር ድንበር ሲያስከብሩ የነበሩ ጀግኖች የክብር መለዮአቸውን ተገፈው፣ ክብራቸው ተዋርዶ በየመንገዱ ለልመና የተዳረጉበት ያ አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የፓርቲ እንጂ የሀገር ተቋም ተደርጎ ባለመወሰዱ የተፈጠረ ጥቁር ጠባሳ ነበር። ይህ ድርጊት የሠራዊቱን ሞራል በእጅጉ የጎዳና ለሀገር የተከፈለውን ዋጋ ያዋረደ ታሪካዊ ስህተት ሆኖ ተመዝግቧል።

የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ግን፣ ይህንን ታሪካዊ ስብራትና ስሁት አሠራር ከመሠረቱ ቀልብሶታል። የመደመር እሳቤ መከላከያ ሠራዊቱ የፓርቲ ወይም የርዕዮተ ዓለም ጠባቂ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ እና የዜጎቿ የጋራ ክብር ዘብ እንዲሆን በአዲስ መልክ በጠንካራ መሠረት ላይ አዋቅሮታል።

የትናንቶቹን በየጎዳናው የተበተኑ የሠራዊት አባላትን ክብር በመመለስና ወረታቸውን በማሰብ፣ "መከላከያ የሀገር እንጂ የፓርቲ አይደለም" የሚለውን መርህ በተግባር አሳይቷል። ዛሬ ላይ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን በጥልቀት በማዘመን፣ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርጎ ተልዕኮውን እንዲያከናውን ተደርጓል።

ይህ ሠራዊት ለሕሊናውና ለሕገ መንግሥቱ ብቻ የቆመ፣ የሕዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል። የተበተነውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እንደገና ዳግም የማቋቋምና የማዋቀር ታሪካዊ ራዕይም የዚሁ ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ፍሬ ነው።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የትናንቱን የአባቶች ወኔና አርበኝነት ሙሉ በሙሉ የወረሰ ከመሆኑም ባሻገር፣ በዘመናዊ ሚሊታሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የታጠቀ ግዙፍ ኃይል ሆኗል። የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና በራስ አቅም በመፍጠር የሀገርን የመከላከል አቅም እጅግ አስተማማኝ ደረጃ ላይ አድርሶታል።

የሠራዊቱን ትጥቅና ስንቅ በአግባቡ በማሟላት፣ ሀገራችንን ከውስጥ ባንዳና ከውጭ የባዳ ጠላቶች በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል የሚችልበት ልዕለ-ቁመና ላይ ይገኛል። መከላከያችን የሰውን አቅም ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር ያገኘው ልቀት እንዲሁም ከሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተውጣጡ ጀግኖችን አቅፎ እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ መልክ ያለው ተቋም መሆኑ፣ የሠራዊቱን ኃያልነት ይበልጥ አጉልቶታል።

በመሆኑም የዛሬው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የደረሰበት የላቀ ግርማ ሞገስና ልቀት፣ የመደመር የሐሳብ ዘር ያፈራው ጣፋጭ የተግባር ፍሬ ነው። የትናንት ጉድለቶችን አርሞ፣ በክብር ወድቀው ሀገር ያቆዩልንን አባቶች አደራ በአግባቡ የተረከበው ይህ ሠራዊት፣ በወታደራዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የቀደመ፣ በሥነ-ምግባር የታነጸ፣ ለሕሊናውና ለሕገ መንግሥቱ ብቻ የቆመ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የኩራት ማማ ሆኖ ይገኛል።

የመደመር መንግሥት ሠራዊቱን የሀገር ኩራትና የሉዓላዊነት ዋስትና አድርጎ በማነጽ፣ የአባቶችን አደራ በአግባቡ የሚወጣ ትውልድ መፍጠሩን በተግባር አስመስክሯል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: