Search

የመደመር መንግሥት፡ የሐሳብ ዘር፣ የተግባር ፍሬ ከእርግማን ወደ ብልጽግና መሠረትነት

ቅዳሜ ነሐሴ 09, 2018 49

ማንኛውም ታላቅ ሀገራዊ ስኬት የሚጀምረው ከጠራና ከረቂቅ የሐሳብ ፅንስ ነው፡፡ የ"መደመር" ፍልስፍና እንደ ሐሳብ ዘር መሬት ላይ ወድቆ በላብና በትጋት ሲኮተኮት፣ ዛሬ ላይ ሀገርን ወደ ብልጽግና ማማ የሚያሸጋግሩ ግዙፍ የተግባር ፍሬዎችን ማፍራት ችሏል፡፡

የመደመር መንግሥት ይህንን የሐሳብ ዘር ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ካስመዘገባቸው ታላላቅ ስኬቶች መካከል፣ የማዕድን እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ህያው ማሳያዎች ናቸው፡፡

የማዕድን ዘርፍ፡- ከእርግማን ወደ ብልጽግና መሠረትነት

ባለፉት ዓመታት የማዕድን ዘርፉ ከነበረበት ግልጽነት የጎደለው አሠራር፣ የኮንትሮባንድ ንግድና የጥቂቶች መጠቀሚያነት ወጥቶ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚውልበት ስትራቴጂካዊ ርምጃ ተወስዷል።

የመደመር መንግሥት ይህንን ዘርፍ ከእርግማን ወደ ልማት መሣሪያነት ለመቀየር በወሰደው ቆራጥ የሪፎርም ርምጃ፣ የማዕድን አስተዳደር ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን አድርጓል።

በተለይም ማዕድናትን በጥሬው የመላክ ኋላቀር ልማድን በመቀየር፣ በሀገር ውስጥ እሴት የሚጨምሩ ፋብሪካዎችንና የወርቅ ማጣሪያዎችን በመገንባት የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል።

በተጨማሪም የዘርፉ ትልቁ ስኬት ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች ያሉ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉ ነው። የሮያሊቲ ክፍያ እና ታክስን ግልጽ እና ፍትሐዊ በሆነ ቀመር ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲከፋፈል በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማሻሻል ተችሏል።

ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ወሳኝ የሆነው የሲሚንቶ ምርት በ2014 ዓ.ም ከነበረበት 6.2 ሚሊዮን ቶን በ2017 ዓ.ም ወደ 9.1 ሚሊዮን ቶን አድጓል። ለዚህም በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ማምረት መግባቱ ትልቅ ድርሻ አለው።

በሌላ በኩል፣ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተደረገው ጥረት፣ አራት የሚጠጉ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካዎች ወደ ምርት ገብተዋል። ለዓመታት የሕዝብ ምኞት የነበረው የካሉብ ጋዝ ሀብትም ወጥቶ ለማዳበሪያ፣ ለትራንስፖርት እና ለኃይል አቅርቦት እንዲውል ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል።

በአጠቃላይ፣ የመደመር መንግሥት በማዕድን ዘርፍ እያስመዘገበ ያለው ስኬት፣ "መደመር" በወረቀት ላይ የሰፈረ ርዕዮት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ መሬት ወርዶ የዜጎችን ሕይወት በተጨባጭ የሚቀይር የሐሳብ ዘር መሆኑን ያረጋግጣል።

የተቀበሩ ማዕድናትን በጥበብ በማውጣት ወደ ብልጽግና ምንጭነት በመቀየር፣  ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም በፈጠራና በፍጥነት ወደ ላቀ የተግባር ፍሬነት ቀይራዋለች። ይህ የትውልድ ዝላይ፣ ዘመኑን የዋጀችና በጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ላይ የቆመች ሀገርን ዕውን የማድረግ ታላቅ ራዕይ ማሳያ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: