Search

በተጋመደ ሕዝብ የጸና ሀገረ መንግሥት፤ የተደመረች ኢትዮጵያ

ቅዳሜ ነሐሴ 09, 2018 52

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ያነሱት አንድ ሐሳብ ነበር። ይኸውም የኢትዮጵያውያን ጥልቀት ያለው ጂኦግራፊና ቋንቋ የማይገድበው የትስስር እና የአብሮነት ማዕቀፍ መሆኑን የሚሞግት እውነት ነው።

ከጎንደር ተነስቶ በአክሱም፣ በላሊበላና በፋሲል በሌሎችም ያነሷቸው የታሪክ አሻራዎች፣ የሕዝቦች ጥብቅ ቁርኝት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህን የታሪክ ሀቅ በጥልቀት ስንመረምረው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝም ብሎ የተገናኘ ወይም የተሳሰረ ብቻ ሳይሆን፣ ፈፅሞ ሊፈታ በማይችል መልኩ "የተጋመደ" ሕዝብ መሆኑን እንረዳለን።

የ"መደመር" እሳቤ ደግሞ ይህንን ነባርና ፅኑ የሕዝቦች መጋመድ እንደ አንድ ጠንካራ ገመድ በመጠቀም፣ የሕዝቦችን ወንድማማችነት ወደ ላቀ የሀገር ግንባታ ኃይል የሚቀይር የዘመናችን የአማካይ መንገድ ነው።

የታሪክ ድርሳናት ሕዝቦቻችን በተለያዩ ዘመናት እንዴት እንደተጋመዱ ጉልህ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በደብረ ታቦር ከተማ በብሔር ኦሮሞ፣ በሃይማኖት ደግሞ ሙስሊም የሆኑት የየጁ መሳፍንት በጎንደር ቤተ መንግሥት ውስጥ ነገሥታት ሆነው ማስተዳደራቸው እና በወቅቱም የቤተ መንግሥቱ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ሆኖ ማገልገሉ የሕዝቦችን ጥልቅ መጋመድ ያሳያል።

በተጨማሪም፣ የቀዳማዊ ዳዊት ልጅ የሆኑት ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ የሀድያ ንጉስ ልጅ የነበረችውን እና በእስልምና እምነት ያደገችውን ንግስት እሌኒን ማግባታቸው፣ የደም እና የእምነት አጥርን ያፈረሰ የታሪክ ትስስር ማሳያ ነው።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያም ቢሆን፣ የጅማ እና የከፋ ነገሥታት ከኦሮሞ ብሔር ጋር ያደረጉት ስርወ-መንግሥታዊ የጋብቻ ትስስር አንዱ የዚህ የተጋመደ ማንነት አካል ነው። በባሌ ደግሞ የኦሮሞ እና የሶማሌ ማኅበረሰቦች በ"መገንታ" ባህላዊ ተቋም አማካኝነት በመከራ ጊዜ መሸጋገሪያ በማበጀት እና አብረው በመኖር የሕዝቦችን የእርስ በእርስ መጋመድ በጉልህ አስመስክረዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሕዝቦች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመንቀሳቀስ፣ አብሮ በመሥራትና ስልጣኔን በማጋራት የተሳሰሩበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የየም ሕዝቦች ወደ ጅማ በማቅናት በንጉሥ ዳግማዊ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ውስጥ በነበራቸው የሥራ ትጋትና ታማኝነት እስከ አጋፋሪነት ማዕረግ መድረሳቸው ነው።

ከዚህም ባለፈ መንገድን ጨምሮ በልዩ ልዩ የግንባታ ሥራዎች ተሰማርተው ንጉሱን በማገልገላቸው የቦታ ርስት ተሰጥቷቸው፣ አብረው ሰፍረው ከኦሮሞው ማህበረሰብ ጋር በቋንቋ፣ በሃይማኖት እና በጋብቻ ተጋምደው ቀርተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የትምህርትና የስልጣኔ ማዕከል የነበረችው ጎንደር፣ በአህመድ አልጋዚ ጦርነት ከደረሰባት ውድመት አገግማ ዳግም የትምህርት ማዕከል እንድትሆን የጉራጌ ሊቃውንት የነበራቸው ጉልህ ሚና የዚሁ ስልጣኔን የመጋራትና በጋራ የመሥራት ማሳያ ነው።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ርቀትን የማይገነዘብ ለመሆኑ ሌላኛው ህያው ማስረጃ፣ የወላይታ ባህላዊ ንጉስ "ትግሬናታ" በሚል መጠሪያ መታወቁ ሲሆን፣ ይህም ከሰሜኑ የትግራይ ሕዝብ ጋር የነበረውን የረዥም ዘመን ታሪካዊና ባህላዊ ጥልቅ ትስስር የሚያሳይ ነው። በሶማሌ ክልል የሚገኙ በርካታ የአፋን ኦሮሞ የቦታ መጠሪያዎችም የዚሁ ድንበር ተሻጋሪ መጋመድ አካል ናቸው።

ኢትዮጵያውያን የገነቧቸው ታላላቅ ስልጣኔዎች የአንድ አካባቢ ወይም ብሔር ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም የተጋመደ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው። ይህ መጋመድ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብሮችም የሰመረ ነው። የንግድ እና የገበያ ልውውጦች ሕዝቡን ከሁሉም አቅጣጫ ሲያስተሳስሩና ሲያቆራኙ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ናቸው።

ለምሳሌ ጨው አሞሌ፣ የዝሆን ጥርስ እና የግብርና ውጤቶች ከአንዱ የሀገራችን ጫፍ ወደ ሌላው እየተለዋወጡ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የባህልም መወራረስን ፈጥረዋል። ከዘይላ እና ከበርበራ ወደብ ተነስተው ወደ ሐረር እና መሃል ሀገር የሚዘልቁት የንግድ መስመሮች የኢሳ፣ የገደቡርሲ፣ የኖሌ እና የጃርሶ ኦሮሞዎችን ከሐረሪ እና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በማስተሳሰር ጥልቅ የንግድና የባህል ልውውጥን አዋልደዋል።

ከዚህም አልፎ በሐረር ጀጎል ግንብ ውስጥ በሚገኙ የሙስሊም አድባራት ሐረሪው፣ ኦሮሞው፣ አርጎባው፣ ሶማሌው እና አፋሩ በጋራ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት መንፈሳዊ ትስስር ገንብተዋል።

ገበያዎቻችን በየትኛውም የሀገራችን ክፍል 'ሰኞ ገበያ'፣ 'ማክሰኞ ገበያ' እየተባሉ በጋራ ስያሜ መጠራታቸው፣ በጉራጌ 'ጆካ'፣ በሲዳማ 'አፈኒ'፣ በወሎ 'አበጋር'፣ በጋሞ 'ዱቡሻ' በሚል የሚታወቁት የሽምግልና ሥርዓቶቻችን እንዲሁም የለቅሶ እና የሰርግ ባህሎቻችን አንዱ ከሌላው የተወራረሱ እና ተመሳሳይ ሆነው መዋቀራቸው የአብሮነት መገለጫዎች ናቸው።

በሃይማኖትም ቢሆን ሙስሊም እና ክርስቲያኑ የአካባቢው ማህበረሰብ የቁልቢ ገብርኤልን በዓል በጋራ ማክበራቸው የጋራ እሴቶቻችን ምን ያህል እርስ በርስ እንደተጋመዱ የሚያረጋግጥልን ህያው ማስረጃ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች መጋመድ በውጣ ውረዶች ውስጥ ተፈትኖ እንደ ብረት የጠነከረ ነው። ይህ የተጋመደ ሕዝብ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ልዩነቶቹን ወደ ጎን በመተው በጋራ ደም አፍስሶ ሉዓላዊነቱን አፅንቷል። በዘመናችንም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከህፃን እስከ አዛውንት ድረስ ያለውን ጥሪት በማሰባሰብ የዘመናት ቁጭትን በአብሮነት አሻራው አትሞ እየገነባ ይገኛል።

ለማጠቃለል ያህል፣ ኢትዮጵያዊነት ልዩነቶች ጠፍተው አንድ ወጥ የምንሆንበት ጠባብ መንገድ ሳይሆን፣ ብዝኃነት በኅብረብሔራዊነት የደመቀበት ታላቅ የአብሮነት ማንነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሰመሩበት፣ ሕዝባችን ዝም ብሎ የተሳሰረ ሳይሆን በእጅጉ የተጋመደ ነው።

የተጋመደ ሕዝብ የገነባት ሀገርም በቀላሉ የማትበጠስ፣ ጽኑ እና የቆመች ናት። ታሪካችን የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፤ የተጋመደን ሕዝብ በምንም አይነት መንገድ መበጠስ አይቻልም።

የመደመር መንግሥት ዋነኛ ተልዕኮም ይህንን በማህበራዊ ውርስ፣ በታሪካዊ ተጋድሎ እና በጋራ እሴቶች የተገመደን የኢትዮጵያውያን ማገር ይበልጥ በማጥበቅ፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ነው፡፡ መደመር ይህን የተጋመደ ኃይል አሰባስቦ፣ ወንድማማችነት የነገሰባትን፣ የማይነጣጠል እጣ ፈንታ ያላትን ጽኑ ሀገር አጽንቶ ለማስቀጠል የሚያስችል አብሮነትን የሚሰብክ የዘመናችን ድንቅ ፍልስፍና ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: