ታዋቂው የአረብኛ ይዘት ፈጣሪ እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አሊ ዳውድ የዓባይ ወንዝ ዋነኛ መነሻ ኢትዮጵያ መሆኗን በአካል በመገኘት ማረጋገጡን አስታውቋል።
አሊ ዳውድ ወደ ማራኪዋ የባሕር ዳር ከተማ ባደረገው የቅርብ ጊዜ ጉዞ፣ የዓባይን መነሻ በዓይኑ ተመልክቶ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተሳሳተ መረጃ እና አመለካከት በተጨባጭ ማረሙን ገልጿል።
ይዘት ፈጣሪው ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር ባደረገው ልዩ ቆይታ እንዳብራራው፣ ከዚህ ቀደም የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውኃ መጠን የሚቀዳው ከኢትዮጵያ እና ከጣና ሐይቅ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ግንዛቤ አልነበረውም።
አሁን ግን እውነታውን በአካል በመረዳቱና የጣናን ግርማ ሞገስ በመመልከቱ፣ ሌሎችም የዓለም ማህበረሰብ ክፍሎች እንዳይሸወዱ እና ይህንን ትክክለኛ መረጃ እንዲያውቁ በስፋት እንደሚሰራ አረጋግጧል።
ይህ ተግባሩ ስለ ዓባይ ወንዝ መነሻ ለዓለም ህዝብ ትክክለኛውን ማስተማሪያ ለመስጠት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
ከ12 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበር ያስታወሰው አሊ ዳውድ፣ አሁን በድጋሚ ሲመለስ በኮሪደር ልማት የባሕር ዳር ከተማ ያሳየችውን አስደናቂ ለውጥና እድገት በእጅጉ አድንቋል።
በጣና ፈርጥ በሆነችው ባሕር ዳር የተሰሩት አዳዲስ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከተማዋን ይበልጥ ውብ እንዳደረጓት የመሰከረ ሲሆን፣ የህዝቡን ልዩ ትህትና እና ማራኪ እንግዳ ተቀባይነት በአድናቆት አወድሷል።
ይህ አጋጣሚ በታሪክ ደረጃ ይታወቁ የነበሩ የውሃ ባለቤትነት ብዥታዎችን ለማጥራት እና እውነታውን ለዓለም ለማሳወቅ ጠንካራ ምስክርነት የሰጠበት ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: