በታርጫ ከተማ "ማንሰራራት ለክልላችን ከፍታ" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ፣ በበጀት ዓመቱ የላቀ ሀገራዊና ክልላዊ ውጤቶች መመዝገባቸው ተገለጸ።.
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ እና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከህዝብ ለሚነሱ የሠላም፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎች ዘላቂ ምላሽ በመስጠት በኩል ተጨባጭ ለውጦች ታይተዋል።
በተለይም የክልሉን ፀጋዎች በተገቢው በመጠቀም በቱሪዝምና ማዕድን ልማት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በግብርና ምርታማነትና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ፣ እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ አበረታች እመርታዎች ተመዝግበዋል።
ከዚህም ባሻገር የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ በፋይዳ መታወቂያ ተደራሽነት እና በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የተሻለ አፈጻጸም የታየ ሲሆን፣ በሁሉም የዞን ከተሞች የተገነቡት የመሶብ አንድ ማዕከላት ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተጨባጭ እየቀረፉ ይገኛሉ።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው፣ በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ ስኬታማነት እስከ ታችኛው መዋቅር የተዘረጋውን የፓርቲውን ጠንካራ አደረጃጀት የሚያሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በቀጣዩ የሥራ ዘመንም የዲጂታላይዘሽን ጉዞውን ይበልጥ ለማሳለጥ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽሉ የመሶብ አንድ ማዕከላትን በሁሉም ወረዳዎች ለማስፋፋት፣ የገበያ ማረጋጋት ሥራዎችን ለማጠናከር እና አጠቃላይ የህዝቡን ብልጽግና ለማረጋገጥ የአመራሩን አቅም በመገንባት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ በጉባዔው አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይህ ለሁለት ቀናት የሚቆየው የፓርቲው አፈጻጸም ግምገማ ጉባዔ፣ ክልሉን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሸጋገር ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑ ታምኖበታል።
በሰለሞን ባረና
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: